የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢራን ሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦቼ ላይ ከባድ ጥቃት ፈፅማለች ስትል ኢራንን ከሰሰች።
” አሳፋሪ” ስትል በገለፀችው በዚህ ጥቃት አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጻለች።
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ መተላለፊያ የመዝጋት እቅዷ አካል አድርገው ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።
ይህም ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ እንዲቻል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እንደሚውል አክለዋል።
የአሜሪካ ጥቃቶች ለሦስተኛ ቀን የቀጠሉ ሲሆን ፕሬዚደንት ትራምፕ ኢራን ‘በከባዱ’ እንደተመታች ተናግረዋል።
የሁለቱ አገራት ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትራምፕ መተለላፊያው ላይ እገዳ መጣላቸውን ተከትሎ ቴህራን የወሽመጡ “ጠባቂ” ሆና ትቀጥለላች ሲሉ ትራምፕ የተጠቀሙትን ቃል በመጠቀም ምላሽ ሰጥተዋል።
የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመቆጣጠር ያለው ውዝግብ የሁለቱን አገራት ጦርነት ለማስቆም ያለውን ጥረት አመንምኖታል።
ሆኖም ትራምፕ አሁንም ቢሆን ስምምነት ማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ውጥረቱ በቀጠለበት በዚህ ወቅትም ነው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን ክሩዝ ሚሳኤሎች ሁለት የአገሪቷን ታንከሮች ዒላማ ማድረጋቸውን የገለፀችው።
በጥቃቱ አንድ ሕንዳዊ የመርከበኞች ቡድን አባል ሲገደል፣ ስምንት መቁሰላቸውን እና የአራቱ ከባድ ጉዳት መሆኑን ጠቅሳለች።
ከተጎዱት መካከል ስድስቱ ሕንዳውያን ሲሆኑ ሁለቱ ዩክሬናዊያን እንደሆኑ የኤምሬስትስ መከላከያ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
“ሚኒስቴሩ ይህንን ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ስምምነቶችን በግልጽ የጣሰውን እና በቀጣናው መረጋጋት እና ፀጥታ ላይ ስጋት የደቀነ ጥቃት ያወግዛል” ብሏል።
BBC
