አውስትራሊያዊው የአክሲዮን ኩባንያ አስካሪ ሜታልስ በኢትዮጵያ የሚገኘውን ትልቅ የኒጆ ወርቅ ፕሮጀክት ለመግዛት ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ። ግዢው ኩባንያው በኢትዮጵያ የማዕድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዲይዝ የሚያስችለው ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ 1,174 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው።
ይህ የተፈፀመው ደግሞ የፕሮጀክቱ ባለቤት ከነበረው ዢንግሹ ማይኒንግ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት የተባለውን ኩባንያ ላይ 100% ድርሻ በመግዛት ነው።
ይህ ግዢ አስካሪ ሜታልስ ባለፉት 4 ዓመታት በኢትዮጵያውያን አጋሮች ሲስተዳደር የነበረውን የኒጆ ፕሮጀክት ላይ ሙሉ ህጋዊ እና የባለቤትነት መብትን የሚያስገኝለት ይሆናል ተብሏል።
የኒጆ ፕሮጀክት በአረቢያ-ኑቢያን ጋሻ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ የበለፀገ የጂኦሎጂካል ክልል በግብፅ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሳውዲ አረቢያ እና የመን በሚገኙ በርካታ ሚሊዮን አውንስ የወርቅ ክምችቶች ይታወቃል።
የኒጆ የወርቅ ፕሮጀክት እንደ ካናዳዊው ማዕድን አውጪ አላይድ ጎልድ ባለቤትነት ስር ያለው የ3.4 ሚሊዮን አውንስ የኩርሙክ ማዕድን ማውጫ እና የኬፊ ጎልድ ኤንድ ኮፐር ባለቤትነት ስር ያለውን የ1.7 ሚሊዮን አውንስ ቱሉ ካፒ ማዕድን ማውጫ በሚያዋስነው ተመሳሳይ የግሪን ስቶን ቤልት ላይ ይገኛል።
