አዲሱ የደሞዝ ማሻሻያ በቀጣይ 10 ቀናት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5 ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ አዲሱ የደመወዝ ጭማሪ በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጀማሉ (ዶ/ር) የደሞዝ ማሻሻያው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ጭማሪ መሆኑን አንስተው፤ የመጀመሪያው ዙር ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ ሰራተኞች ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የአሁኑ የደሞዝ ማሻሻያ ግን የመንግስት ተሿሚዎችንና ተመራጮችን ጨምሮ ሁሉንም ሰራተኛ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሄም የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ የሪፎርም ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል፡፡
በከተማ ደረጃ ለሁሉም ተቋማት ወደተግባር እንዲገቡ አቅጣጫ የተቀመጠ መሆኑን አንስተው፤ አዲሱ የደሞዝ ማሻሻያ በዚህ ሳምንት ግፋ ቢል እስከ ጥቅምት 15 ወደተግባር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጣ_ፕላስ
