አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ ሆነ

Date:

በቅርቡ 75ኛ የምስረታ በዓሉን ያከበረው አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚውን ደረጃ መያዙን ጥናትን ጠቅሶ አፍሪካን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።

በ”QS World University Rankings” መሰረት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት፣ በምርምር ስራዎች ተፅዕኖ እና በቀጣናዊ ተጽዕኖው ባሳየው የላቀ ብቃት መሪነቱን ሊረከብ ችሏል።

እ.ኤ.አ.በ1950 የተመሰረተው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ አንጋፋ እና ስመ-ጥሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲሆን፣ ለበርካታ ዓመታት የሀገሪቱ የእውቀት እና የጥናት ማዕከል ሆኖ ማገልገሉ ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይም በሰብአዊነት፣ በማህበራዊ ሳይንስ፣ በምህንድስና እና በጤና ሳይንስ ዘርፎች ባለው ጠንካራ የትምህርት አሰጣጥ ይታወቃል ያለው ዘገባው፤ የተቋሙ የምርምር ተቋማት በሕዝብ ጤና፣ በግብርና እና በአካባቢ ጥናት ላይ የሚያደርጓቸው ጥናቶች ለሀገራዊ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብሏል።

ከአካዳሚክ ስራው ባለፈ ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ምሁራዊ ታሪክ ውስጥ የነበረው ሚና በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ተቋም እንዲሆን እንዳስቻለው ተገልጿል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የ #ኡጋንዳው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ “የአፍሪካው ሀርቫርድ” በሚል መጠሪያ ይታወቃል ሲል አፍሪካን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።

በ1922 እ.ኤ.አ. የተመሰረተው ይህ ተቋም በአህጉሪቱ ካሉ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን በህክምና፣ በሕዝብ ጤና እና በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ዓለም አቀፍ እውቅናን አትርፏል። ማኬሬሬ በርካታ የአፍሪካ ፕሬዝዳንቶችን፣ ዝነኛ ደራሲያንን እና ምሁራንን ያፈራ ተቋም ከመሆኑም ባለፈ፣ በቀጣናዊ ትብብር እና በምርምር ስራዎቹ የላቀ ስም አለው ተብሏል።

የ #ኬንያው ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ በቀጣናው ካሉ ዋና ዋና የምርምር ማዕከላት አንዱ መሆኑን አረጋግጧል። ዩኒቨርሲቲው በተለይም በሕግ፣ በምህንድስና እና በኢኮኖሚክስ ዘርፎች ባሉት ጠንካራ የትምህርት ፕሮግራሞች የሚታወቅ ሲሆን፣ በኬንያ የፖሊሲ ቀረፃ እና ሙያዊ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ዘባው አመላክቷል።

በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የ #ሱዳኑ ካርቱም ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ካለችበት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት አኳያ ይህን ደረጃ መያዙ የተቋሙን ጥንካሬ የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል። እነዚህ አራት ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው እውቅና የምሥራቅ አፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ውጤታማነቱን እያሳደገ መምጣቱን የሚያመለክት ነው ተብሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...