‹‹አፀፋ ጋዜጠኝነት›› ማለት አንድ ሰው በጻፈው ጽሑፍ ላይ የድጋፍ ወይም የተቃውሞ አስተያየት የመሥጠት ልምድ ማለት ነው፡፡ አንድ ሐሳብ በአንድ ሰው ተጽፎ ትክክል ይሁንም የተሳሳተ መጀመሪያ በተጻፈው ሐሳብ ላይ ሌላ ምንም አስተያየት ካልተሠጠ መጀመሪያ የተጻፈው ሐሳብ ትክክለኛ ወይም ገዢ ሐሳብ ይኾናል ማለት ነው፡፡ በዶ/ር ዐቢይ የሥልጣን ዘመን እስከ አሁን ከነበሩት መንግሥታት በተሻለ መልኩ ሐሳብን መግለጽ የተቻለ ቢኾንም በመንግሥት በኩል በተጻፉት ሐሳቦች ላይ የአፀፋ ሐሳብ የማቅረብ ልምድ ባለመኖሩ በዜጎች የተጻፉ ሐሳቦች ሕብረተሰቡን የመግዛትና የመምራት አቅም አላቸው፡፡ አንድ በተጻፈ ሐሳብ ላይ የአፀፋ ሐሳብ ሲጻፍ ሕብረተሠቡ አማራጭ ሐሳብ ስለሚያገኝ ግንዛቤውን ለማሣደግ በእጅጉ ይረዳል፡፡ የአፀፋ ሐሳብ መኖር በመረጃ የበለፀገ ማሕበረሰብ ለመፍጠርና አገሪቱን ወደ ሥልጣኔ ለመውሰድ አንዱና ትልቁ አማራጭ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት የአንድ አገር ዜጎች በተለያየ አስተሳሰቦች ምክንያት ጦር ሜዳ ሄደን እርስ በርሳችን እየተዋጋን ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ደግሞ የሠው ሕይወትና ንብረት እየወደመ ነው፡፡ በሚዲያ ግን ጦርነት ብንገጥም ዕውቀትና አዳዲስ ሐሣብ እንጂ የሚደርስ ምንም ዐይነት ሰዋዊም ሆነ ቁሳዊ አደጋ የለም፡፡ በሰለጠነ መንገድ የተለያየ ሐሳባችንን በሚዲያ ማስተናገድ አቅቶን በጦር ሜዳ ማስተናገዳችን የሠለጠነ ሠው ለመሆን ገና ብዙ እንደሚቀረን ያሳያል፡፡ ብዙ ምሁራን በትምህርት፣ በማንበብ እና በሥራ ልምድ ያጠራቀሙትን ዕውቀት ወደ ገንዘብ ብቻ ለመለወጥ ይጥራሉ እንጂ፤ ወይ በጋዜጣ፣ አልያም በመጽሔት እየጻፉ ዕውቀታቸው ለሌሎች ለማስተላለፍ አይጥሩም፡፡ ወይ ደግሞ ሌሎች በጻፉት ሥራ ላይ የአጸፋ መልስ በመስጠት አንባቢያን በቂ መረጃ እንዲያገኙ አይጥሩም፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ዓይነት ሥራ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስለማያስገኝ ብዙ ሰዎች ጽሑፍ በመጻፍ ጊዜቸውን አያባክኑም፡፡
መንግሥት መረጃ በሰላማዊ መንገድ መለዋወጥ ለአንድ አገር እድገት ያለውን አበርክቶ ተገንዝቦ ለሙያው ድጋፍ ቢያደርግ አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በእጅጉ ባስቻለ ነበር፡፡ በአገራችን አንድም ባለሐብት ሚዲያን የሚደግፍ የለም፡፡ እርግጥ ነው በአገራችን በጤነኛ መንገድ ሐብት ያፈራ ባለሐብት ማግኘትም አስቸጋሪ ነው፡፡ በተጨማሪ በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ባለሐብቶች የሌሉ በመኾኑ ለአገር የሚጠቅመውን ነገር ከማሠብ ይልቅ ትርፍ ብቻ የሚያስገኘውን ንግድ ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የብዙ ዜጎች ትግልና መስዋዕትነት ያመጣው አዲሱ መንግሥት አገር የሚያስተዳድረው ከህወሓቶች የወረሰውን አሠራር አንድም ሳይለውጥ በመኾኑ በፊት የነበረው ችግር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ ድሮም አሁንም ለኢትዮጵያውያን ሳይኾን ለጥቂት ባለሥልጣናት እና ለተከታዮቻቸው ብቻ ነው ምቹነቷ፡፡ የዐቢይ መንግሥት አንድ ጠቅላይ ሚንስትር መሥራት የሚገባውን ሥራ ትቶ እራሱን የሚያስደስተውን ሥራ ላይ ብቻ ተጠምዶ ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ተረስቷል፡፡
አሁን አገራችን ያለችበትን አስቸጋሪ ጊዜ ለመወጣት ማንኛውም ምሁር ነኝ የሚል ሁሉ ወይ እራሱ ሐሳብ እያመነጨ መጻፍ አለያም ደግሞ ሌሎች በሚጽፉት ላይ የአፀፋ መልስ በመስጠት ዜጎች በቂ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ጦር ሜዳ ሂዶ ከመዋጋት የተሻለ አርበኝነት ነው፡፡ እኛ የምናቃቸው ሁሉም መንግሥታት ሐሳብ እያመነጩ ሕዝብን መረጃ ለማስጨበጥ የሚጥሩ ዜጎችን ማሰር ይቀናቸዋል እንጂ ለመደገፍ ሲሞክሩ አይታዩም፡፡ በተቃራኒው አሸባሪዎችና የአገርን ሐብት በሚያስፈራ ደረጃ የዘረፉ ዜጎችን መለማመጥና በሰላም እንዲኖሩ መፍቀድ በተደጋጋሚ መንግሥት ሲሰራው የነበረ ተግባር ነው፡፡ በተለይ እጅግ የገዘፈ ማዕረግ ያላቸው ምሁራን አልፎ አልፎ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ እጅግ የተለሣለሠ፣ በተጨባጭ በአገሪቱ ውስጥ ካለው ችግር ጋር የማይሄድ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን መንግሥት የሠራውን ስሕተት በድፍረት ለመግለጽ አቅም ኖሯቸው አያውቅም፡፡ አንድ ግለሰብ የተሳሳተ ሥራ ቢሠራ በዋናነት እራሱን ነው የሚጎዳው፡፡ አንድ ያገር መሪ ግን ጥሩ ሥራ ከሠራ ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የተሣሣተ ውሳኔ ከወሰነ ደግሞ ሚሊዮኖች ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በመኾኑም አንድን ያገር መሪ እግር በእግር እየተከታተሉ የሠራውን መልካም ተግባር ማድነቅ ማበረታታት፤ የሠራውን የተሣሣተ ሥራ ደግሞ ያለ ምንም ማመንታት መተቸት ከእያንዳንዱ ምሁር የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በሰሜኑ የሐገራችን ክፍል ሕግ በማስከበር ዘመቻ መንግሥት በአጭር ጊዜ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ እንዳወጣ ነግሮናል፡፡ በሰላሙ ጊዜ ሕብረተሰቡ በሚዲያ አማካኝነት በቂ መረጃ እንዲያገኝ የማስተማር ሥራ ቢሠራ እንዲህ ዓይነት እልቂት ውስጥ ባተገባ ነበር፡፡
ጋዜጣና መጽሔት የሚጻፈው በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ በሌሎች ቋንቋዎች በመንግሥት ድጋፍ በርካታ የሚዲያ ሥራ ቢሠራ የአገራችንን ሕዝቦች ብቃትና ችሎታ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ በተቻለ ነበር፡፡ ፈርሶ የነበረው የኮሚኒኬሽን ሚንስትር አሁን የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ተብሎ እንደገና ተቋቁሟል፡፡ ነገር ግን ይህ መሥሪያ ቤት የሚዲያ ሰዎችን ከማዋከብ ውጭ ሚዲያው እንዲያድግ ምንም ሥራ ሠርቶ አያውቅም፡፡ ጋዜጠኞች የተሳሳተ ነገር ወይም መጽሔት ላይ የአፀፋ ጋዜጠኝነት ሥራ ሠርቶ አያውቅም፡፡ መንግሥት ቢያንስ ቢያንስ የራሱን አቋም ለሕዝብ በተለያየ ቋንቋ የሚያስረዱት ሙያተኞች እንኳን ማሠማራት እንደሚጠቅመው መገንዘብ አለበት፡፡ ብዙ ሠው አዲስ ዘመን ጋዜጣን ወይም ኢቢሲን ስለማይከታተል መንግሥት አቋሙን ሕዝብ እንዲያውቅለት የግሉን እና ብዙ አንባቢ ያላቸውን የሚዲያ ተቋማት በመጠቀም ከሕዝብ ጋር ግንኙነት ቢያደርግ ዓላማውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ በተሻለ ሁኔታ ያስችለዋል፡፡
በመንግሥት አመራር ውስጥ ያሉ ምሁራን ነን የሚሉ ግለሰቦች አንዳቸው ሐሳባቸውን እየጻፉ ከሕዝብ ጋር ግንኙነት አያደርጉም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ስለሚያስተዳድሩት ተቋም እንኳን ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል የሚሉትን ነገር ለሕዝብ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ለማሣወቅ አይጥሩም፡፡ ለምሣሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትኩረት በእጅጉ የሳበውን የዓባይ ግድብ ፕሮጀት ቢያንስ በየወሩ ስለተካሄዱ የሥራ ሂደቶች ባጭሩ ለሕዝብ ለመግለጽ እንኳን የሚጥር በለሥልጣን የለም፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በየጊዜው ምን እየተከናወነ ነው? ጥሩ ነገር ወይስ መጥፎ ነገር? ባለሥልጣናት አንድ ጉዳይ ላይ ቢጽፉና ነዋሪዎች ደግሞ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት ቢጽፉ ሕዝብ ታማኝ የኾነ መረጃ ስለሚያገኝ ለአገር ሰላምም ልማትም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በምዕራቡ ዓለም አፀፋ ጋዜጠኝነት በእጅጉ የተስፋፋ በመኾኑ አንድ ጉዳይ ሲከሰት ያንን ጉዳይ ሁሉም ሚዲያዎች እየተቀባበሉ ስለሚያስተጋቡት ዜጎች እጅግ ተአማኒ የኾነ መረጃ ያገኛሉ፡፡
ለምሣሌ ከወራት በፊት በምዕራባውያን የተገዙ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውሸት ዜና እየተቀባበሉ በማራገብ ላይ ነበር የሰነበቱት፡፡ የገንዘብ አቅም ስላላቸው ዓለማቸውን ለማስፈፀም ጥረዋል፡፡ በጣም የገረመኝ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን እንደመጣ የቅርብ ጓደኛ እስኪመስሉ ድረስ እዚህ አዲስ አበባ መጥቶ የነበረው የኳታሩ መሪ (አልጀዚራ የሚገኝበት አገር) አሁን ለዶ/ር ዐቢይ ጀርባውን ሰጥቶ ሀገር የሚያፈርስ የሐሰት ዜና ሲያሰራጭ ማየቴ ነው፡፡ ይህ ሠው ከፍተኛ የሚባል የገንዘብ ድጋፍ ለዐቢይ እንዳደረገ ሁሉ ሠምተናል፡፡ በአሁኑ ዘመን የሚዲያ ተፈላጊነት በእጅጉ በማደጉ የመረጃ መለዋወጫ ብቻ ሳይኾን ሚዲያ ጦር ሜዳ እየመሰለ ነው፡፡ ብዙ መንግሥታት የተቻላቸውን ሁሉ አድርገው የያዙት ሐሳብ በሚዲያ የበላይ እንዲኾን ይጥራሉ፡፡ ሐሳብን በሚዲያ እየሸጡ ተሰሚነትን ማግኘት የበላይ ለመኾን በእጅጉ ይረዳል፡፡ በሚዲያ ደግሞ ሐሰቡን መሸጥ ያልቻለ ተቋም ወይም ስብስብ የመውደቅ እድሉ በጣም ሠፊ ነው፡፡
የአንድ አገር መሪ ምንም ያህል ተግቶ ቢሠራ አንድን ድሐ አገር ባጭር ጊዜ ወደ ብልጽግና ለመውሰድ አይችልም፡፡ ነገር ግን እንዴት አድርጎ ወደ ብልጽግና እንደሚወስዳት ሚዲያን በመጠቀም ለሕዝብ ማሳወቅ ይችላል፡፡ ምሁራን ደግሞ ከሥር ከሥር እየተከታተሉ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ነው ጤነኛ የኾነ የብልጽግና ጉዞ ነው፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ ወደ ብልጽግና እወስዳችኋለሁ እያሉ እየሰበኩን ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ብልጽግና እንዴት እንደምንጓዝ ፍኖተ ካርታውን ዶ/ር ዐቢይ እንኳን የሚያቁት አይመስለኝም፡፡ እኛም የሰማነው ነገር የለም፡፡ ደግሞስ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ሕገ መንግሥትና የፌደራል ሥርዓት ይዘን እንዴት አድርገን እንደምንበለጽግ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ምክንያት እጅግ የሚደንቅ ተቀባይነትን አግኝተው ነበር፡፡ ኾኖም በሂደት ግን በሚያሣዝን ሁኔታ ተቀባይነታቸው እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ጠባብ ብሔርተኞችን በሥራቸው አሠልፈው እስከያዙ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባውን ሰጥቶ ይቆያል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከፊት ለፊቷ ከባድ ጠላቶች አሏት፡፡ ከፊት ለፊት ያለው ጠላት ጠባብ ብሔርተኞች እና ፀረ የኢትዮጵያና ፀረ አማራ ዓላማ የሚያራምዱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ዜጎች ናቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ እነዚህን ጠላቶች ከፊትና ከኋላ አሰልፎ በተአምር ወደ ብልጽግና መገስገስ እንዲሁም ሀገር አረጋግቶ መምራት አይችልም፡፡ የግድ እነዚህን ጠላቶች መጀመሪያ ማጥራት አለበት፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ግን ይህንን ለማድረግ ፍላጎቱም እቅዱም የለውም፡፡ በኦሮሞ ብሔርተኞች እና በትግሬ ብሔርተኞች መካከል የዓላማ ልዩነት የለም፡፡ ያለው ልዩነት እኔ የበላይ ልሁን የሚል ፉክክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔርተኞች በአሁኑ ጊዜ በሁለት ልብ ተከፍለዋል፡፡ የመጀመሪያው አስተሳሰብ “ክልላችን ገንጥለን የራሳችን መንግሥት መሥርተን ያለንን የተፈጥሮ ሐብት ለራሳችን ብቻ እንጠቀም” የሚል ቅዥት ሲኾን ሁለተኛው አስተሳሰብ ደግሞ “ኢትዮጵያ ያላትን ዘርፈ ብዙ የተፈጥሮ ሐብት በብቸኝነት እንጠቀመው” የሚል ነው፡፡ የትኛውም ክልል እነዚህን ሁሉ ጽንፍ የረገጡ አስተሳሰቦችን በአንድ ላይ ማራመድ እንደማይችል ያቀዋል፡፡
በመኾኑም የብሔር ፖለቲከኞች ልባቸው ለሁለት ተከፍሎ በመቃዥት ላይ ናቸው፡፡ አንድ አገር ውጤት አምጥታ የዜጎቿን ሕይወት ለመለወጥ የግድ ሁለት ነገሮችን አሟልታ መገኘት አለባት፡፡ የመጀመሪያው እጅግ ምርጥ የኾነውን፣ የዜጎችን ሕይወት ሊቀይር የሚችለውን ሐገራዊ ሥርዓት መዘርጋትና በሁሉም ዘርፍ ማለት በሕገ መንግሥት፣ በፌደራል ሥርዓት፣ በመሬት አስተዳደር ወዘተ ተቀባይነት ያለው ሐገራዊ ሥርዓት ባለቤት መኾን ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ያንን ሐገራዊ ሥርዓት የሚመራ ብቃት ያለው ግለሰብ ወይም ፓርቲ ማግኘት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሁለት ነገሮች የላትም፡፡ ለዚህ ነው ማለቂያ ወደሌለው ችግር ውስጥ እየገባን ያለነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሥርዓት እጦት ውስጥ ያለች ሐገር ነች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም አገሩን የሚወድ ዜጋ የግድ ፖለቲከኛ መኾን አለበት፡፡ ፖለቲካው ታሟል፤ ተረባርበን ማዳን አለብን፡፡ አፀፋ ጋዜጠኛ ለመኾን ሁላችንም እንገደዳለን፡፡ ችግር ቤታችን እስኪመጣ ቁጭ ብለን መጠበቅ የለብንም፡፡
