ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ (አይአርሲ) ይፋ ባደረገው የ2026 ዓመታዊ የድንገተኛ አደጋ መከታተያ ዝርዝር መሠረት፣ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ስጋት ውስጥ ካሉ 10 የዓለም አገራት መካከል በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች፣ የቀጣናው አለመረጋጋት እና ተደጋጋሚ የአየር ንብረት ለዉጦች ተዳምረው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጡ ይገኛሉ።
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የሰላም ሁኔታ ደካማ መሆን እና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭት ለዜጎች መፈናቀል እና ለኑሮ መቃወስ ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
ከጸጥታ ችግሮች በተጨማሪ፣ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድጋፎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸው ቀውሱን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው ተገልጿል። በተለይም በ2025 ከዩኤስኤይድ የተደረገው የ387 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅነሳ በ2026 የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተተንብዮአል።
ይህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የምግብ አቅርቦት የሚያስተጓጉል ከመሆኑም ባለፈ፣ ለ650 ሺህ ሕፃናት እና እናቶች የሚቀርበውን የአልሚ ምግብ ሕክምና አደጋ ላይ እንደሚጥል ተመልክቷል።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሱዳን፣ ፍልስጤም (ጋዛ) እና ደቡብ ሱዳን እንደ ቅደም ተከተላቸው ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ሄይቲ አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በአጠቃላይ በዝርዝሩ የተካተቱ 20 ሀገራት የዓለምን ህዝብ 12% ብቻ የሚወክሉ ቢሆኑም፣ 89% የሚሆነውን የዓለም ሰብአዊ እርዳታ ፈላጊ እና ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የዓለም ድሃ ህዝብ የሚይዙ መሆናቸው ተጠቁሟል።
capital news
