በኢትዮጵያ ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች የተሟላ ግንዛቤ ያላቸው ወጣቶች ቁጥር ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ እና 70 በመቶ የሚሆኑት በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው ተገለጸ፡፡
የኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶሎሳ ኦላና፤ ይህ አሐዝ የተገለጸው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2024 ባካሄደው ጥናት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶሎሳ አክለውም፤ “በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚታየው አጠቃላይ የኤች አይ ቪ ስርጭት 30 በመቶውን የሚሸፍኑት አፍላና ወጣቶች ናቸው” ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያካሄደው ጥናት ‘ከትምህርት ቤት ውጭ ያሉ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆነ ታዳጊዎች እና ሕጻናት መካከል 29 በመቶዎቹ የሚሆኑት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይጀምራሉ’ ያለ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 42 በመቶ የሚሆኑት ከአንድ በላይ የፍቅር ጓደኛ እንዳላቸው መረጋገጡን ይገልጻል፡፡
ጥናቱ በተጨማሪም ግንኙነት ከሚፈጸሙት ወጣቶች ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ ወይም 55 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ኮንዶም እንደማይጠቀሙ አመላክቷል።
“ጥናቱ ወጣቶች ለጥቃት እና ለጎጂ ልማዶች ያላቸውን ተጋላጭነትም ዳስሷል” ያሉት አቶ ቶሎሳ፤ 27 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው እንዲሁም 14 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የአልኮል መጠጥ እንደሚጠጡ መረጋገጡን አንስተዋል፡፡
የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አክለውም፤ ማዕከላቸው ይህን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለያዩ የሕክምና ማዕከላት በኩል ሰፊ የማስተማርና የድጋፍ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወጣቶችን ለኤች አይ ቪ ኤድስ እንደሚያጋልጡ ከተለዩ ምክንያቶች መካከል የግንዛቤ እጥረት፣ አሉታዊ የአቻ ግፊትና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
እንዲሁም የመከላከልና መቆጣጠር ሥራው በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረጉት ምክንያቶች ደግሞ፤ የወጣቶች ስብዕና ማበልጸጊያ ማዕከላት በቂ አለመሆን፣ የሚዲያዎችና የሐይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዩን በትኩረት አለመስራታቸው ነው ተብሏል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
