ኢትዮጵያ እና ዴንማርክ ከጎርጎሮሳውያኑ 2025 እስከ 2029 ድረስ ለአምስት ዓመታት የሚዘልቅ የ238.4 ሚሊዮን ዶላር የሁለትዮሽ የልማት ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል እያደገ የመጣውን አጋርነት ያሳያል ተብሏል።
ለአምስት ዓመታት ለሚዘልቀው ፕሮግራሙ 238.4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ከዴንማርክ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የልማት እርዳታ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ መሆኑ ተመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመረታ ሰዋሰው ፕሮግራሙ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ በሆነ ወቅት ላይ መምጣቱን ጠቅሰው፥ ዴንማርክ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ በበኩላቸው ደግሞ ስምምነቱ በኢትዮጵያና ዴንማርክ መካከል ያለውን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ለዓመታት የዘለቀውን መልካም አጋርነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
