ፓርቲው ሰኔ 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም ባከናወነው ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ፓርቲውን የሚመሩ አመራሮችን መምረጡ የሚታወስ ሲሆን፤ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ ፓርቲውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም አዱሱ የፓርቲው ሊቀመንበር ከአሐዱ መድረክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሀገርን ለማፅናት የሚያስችሉ ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው፤ “እንደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ያሉ ተቋማትን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደሆነ ነው የምንረዳው” ብለዋል።
“ነገር ግን በክልሎችና በመንግሥት መካከል የሚደረግን ጦርነት ፓርቲው አልደገፈም፤ አይደግፍም” በማለት ተናግረዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ዜጎች ‘መብታችን አልተከበረም’ እንዲሁም ‘በሠላማዊ መንገድ የምናደርገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አድማጭ አላገኘም’ በሚል ‘ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ትግል መፈታት የሚችለው፤ በሠላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑንም የፓርቲው ሊቀመንበር ገልጸዋል።
አክለውም፤ ኢዜማ ከተመሠረተበት ዓላማ አንፃር የሚጠበቅበትን ያህል አልሰራም” ያሉ ሲሆን፤ “ኢዜማ ሲመሠረት የዜግነት ፖለቲካ፣ ማህበራዊ ፍትሕና ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም በሦስቱም መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ ጠንካራ ስብስብ የነበረው ቢሆንም የሚጠበቅበትን ያክል አልሰራም” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ የፖለቲካ አንዱ ስብራት የሆነውን ‘ፓርቲና መንግሥት አይለይም’ የሚለውን አስተሳሰብ እንዴት እንፍታው ብለው፤ የድርጅትና የመሪ አደረጃጀት የሠሩ ሰዎች ቢኖሩም ነገር ግን አንድነት ያለው የፖለቲካ ባህል ያለው አመራር መፍጠር ግን አልተቻለም፤ ይህም የፓርቲው ድክመት ነው” ሲሉ ዶክተር ሙሉዓለም ገልጸዋል።
“የፓርቲው ድክመት ናቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች እየለየን ለመፍታት ሞክረናል” በማለትም አክለዋል።
”በሀገራችን የተለመደው የፖለቲካ ባህል ስህተት ነው” የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ ከፓርቲው አዲስ የፖለቲካ መንገድ መራመድ የሚጠበቅ በመሆኑን ጠቁመዋል።
“በፓርቲው ውስጥ የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም የሚያግባባን ነገር ላይ ማተኩር ይገባል” ያሉም ሲሆን፤ “ፖለቲከኞች በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያየ የፓለቲካ ፓርቲ ውስጥም ሆነው ‘ጠንካራ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ይኑር!’ በሚለው እና ሠላማዊ የትብብር መንፈስ ላይ ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል።
“በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ከጦርነት ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን እንግልት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ግፍና መከራ እንዲቆም ድምፅ መሆናችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ዶክተር ሙሉዓለም ገልጸዋል።
(አሃዱ)
