የኢትዮቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታል እና ከዚያም ባሻገር 2028” (Leadthe Future: Digital and Beyond 2028) የተሰኘውን የሶስት ዓመታት ስትራቴጂ ሁለተኛ ዓመት የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ የቢዝነስ እቅድ ሐሙስ ነሐሴ 28 2018 ዓ.ም በዝርዝር አቅርበዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ እንደ ገለጹት “የስትራቴጂያችን ዋነኛ ግብ ኩባንያችንን ከመደበኛ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ወደ ሁለንተናዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያ(Telco-to-TechCo) ማሸጋገር ነው” ብለዋል።
የመጪው አመት የገቢ እድገት ለማሳካት በተለይ ከቴሌ ብር ፣ ከክላውድ አገልግሎት ፣ እንደ ዘመን ገበያ ካሉ የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና ተያያዥ ቢዝነስ ምንጮች የተለያየ መጠን ያለው ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት እቅድ ተይዟል፡፡
ተቋሙ ከአለም አቀፍ ቢዝነስ ማለትም የመሰረተ ልማት ማጋራት አገልግሎት ከአለም አቀፍ የሃዋላ አገልግሎት ከ253 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ነው ብሏል፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 43.1 ቢሊዮን ብር የትርፍ ክፍፍል ለማበርከት እና 83.8 ቢሊዮን ብር ግብር ለሀገር ገቢ ለማድረግ ማቀዱን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አሳውቀዋል ።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ኩባንያው በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ አመታዊ ገቢው 295 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ36.7 በመቶ ወይም የ79.2 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ተብሏል።
ከዚህ ገቢ ውስጥ 26.3 በመቶው (77.45 ቢሊዮን ብር) ከዲጂታል እና ተያያዥ የቢዝነስ ዘርፎች የሚገኝ ነው።
በተጨማሪም 253.7 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማመንጨት መታቀዱንም ተገልጿል።
የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች ቁጥር 96.2 ሚሊዮን ያደርሰዋል ። የሞባይል ድምፅ ተጠቃሚዎች 92.3 ሚሊዮን፣ – የሞባይል ዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 60.01 ሚሊዮን፣ – የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኞች ደግሞ 1.26 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል።
በሌላ በኩል የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን 67.69 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን በቴሌብር የሚከናወኑ ግብይቶች መጠን 7.4 ትሪሊዮን ብር እንዲሁም የግብይት ብዛት 4.99 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ እቅድ ተይዟል።
በቴሌ ብር በኩል የሚሰጠው የዲጂታል አነስተኛ ብድር አቅርቦትም ከ19.51 ቢሊዮን ብር ወደ 35.04 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ይደረጋል ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አስረድተዋል።
መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ በበጀት ዓመቱ 5 ሺህ 417 አዳዲስ የ4ጂ ጣቢያዎችን በመገንባት የ4ጂ ኔትወርክን ሽፋን ከ82.23 በመቶ ወደ 95 በመቶ ለማሳደግ ተቋሙ አቅዷል።
የ5ጂ አገልግሎትንም ተደራሽ የሚደረግባቸውን ከተሞች ቁጥር ከ33 ወደ 73 በማሳደግ የጣቢያዎቹን ቁጥር 648 ለማድረስ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለው ብሏል፡፡
የገጠር ተደራሽነትን ለማስፋት 1,685 አዳዲስ ሳይቶችን በመገንባት 4.5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል።
በበጀት አመቱ የዓለም አቀፍ የመረጃ መተላለፊያ(International Gateway) አቅምም ወደ 5.2 Tbps ከፍ ይላል ተብሏል።
ኩባንያውበተጨማሪም 2.6 ሚሊዮን የኮኔክቲቪቲ ዲቫይሶችን ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን የሚሆኑት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ክላውድ ቤዝድ “ዘኔክሰስ” (Nexus)ስማርት ስልኮች ናቸው ተብሏል።
