የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመላው አፍሪካ የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት የ1 ቢሊዮን ዶላር ‘AI for Development’ አርቴፊሻል አስተውሎት ለልማት የተሰኘ አፕሮጀክት ይፋ አድርጋለች፡፡
ይህ ተነሳሽነት የዲጂታል መሠረተ ልማትን በማጎልበት፣ የመንግስት አገልግሎቶችን በማሳደግና ምርታማነትን በማሻሻል በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።
ይህ የተገለፀው የአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ኤች.ኤች ሼክ ካሊድ ቢን ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በG20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም ዘላቂ እድገትን በሰፊ አለም አቀፍ አጋርነትና በማደግ ላይ ባሉ ኢኮኖሚዎች ውስጥ ልማትን የሚደግፉ የፋይናንስ መፍትሄዎችን ለማቅረብ ኤምሬቶች ያላትን ቁርጠኝነትን አረጋግጠዋል።
ውጥኑ የአቡዳቢ የልማት ፈንድ አካል በሆነው በአቡ ዳቢ ኤክስፖርት ጽህፈት ቤት (ADEX) ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ እርዳታ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
ይህ አጋርነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከላቁ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሀይልን ሁለንተናዊ እድገትን እንዲደግፉ በማስቻል ኤሚሬቶች የምትጫወተውን ሚና ያሳያል ተብሏል።
የAI ለልማት ተነሳሽነት በአፍሪካ ሀገራት የሚተገበርና ኢሚሬቶች ለአህጉሪቱ የምታደርገው ሰፊ የውጭ እርዳታ አካል መሆኑ ተነግሯል፡፡
