ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚዋ፣ ሉአላዊነቷና ደህንነቷ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት እስራኤል ታምናለች ያሉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራም ንጉሤ ፤ እስራኤልም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት በዲፕሎማሲና በሰላማዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ያሉት አምባሳደር አቭራም፤ ሁለቱ ሃገራት ጥንታዊና ልዩ የሆነ የብዙ አመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህኛው ዘመንም ሁለቱ ሀገራት የሚተባበሩና የሚረዳዱ ናቸው ብለዋል፡፡
“በአለም አቀፍ መድረክም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር እስራኤል ኢትዮጵያን ትደግፋለች፤ ኢትዮጵያም እስራኤልን ትደግፋለች፤ ይህ መደጋገፍ ግን በኢኮኖሚውም በጤናውም በግብርናውም ጭምር ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡
የእስራኤል ፓርላማ አባል የሆኑት ዶ/ር ጸጋ ፋንታሁን በተመሳሳይ፤ “ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የማግኘት መብቷ የተጠበቀ ነው” ብለዋል፡፡
በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ በበኩላቸው፤ “በእስራኤል በኩል ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋን የመቃወም አዝማሚያ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ እንደገና መልሳ ወደ ቀይ ባሕር ጠረፍ ብትመጣ አንደኛ ወዳጅ ሀገር ናት፤ በተጨማሪም እስራኤል ኢትዮጵያን መግቢያ በር አድርጋ ስለምትመለከታት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንድታግዛት ትፈልጋለች” ብለዋል።
ኢትዮ ኤፍኤም-
