እቴጌ ተዋበች ዓሊ

Date:

ዓይናለም ደበበ

እቴጌ መነን ጦራቸውን አሰልፈው መሐመድ ዓሊ ከተባለው የቱርክ የጦር መሪ ጋራ በድንበር አካባቢ በመፋለም ላይ እንዳሉ፣ የ 15 ዓመት እድሜ ላይ የነበሩት የልጅ ልጃቸው በጦርነቱ ላይ ተማርከው ተወሰዱ። በኋላ አፄ ቴዎድሮስ በሚል የንግሥና ስያሜ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሆኑት መይሳው ካሣ ከእቴጌ መነን ጦር ጋር ተሰልፈው ጠላትን በመፋለም ላይ ነበሩና የእቴጌ መነንን የልጅ ልጅ መማረክ እንደሰሙ ያለአንዳች ረዳት ብቻቸውን ሆነው ሽምጥ እየጋለቡ ሰተት ብለው ከጠላት ሰፈር ገቡ። በተጠንቀቅ የቆሙትን የቱርክ ወታደሮች በጀግንነት አልፈው ከምርኮኛዋ ዘንድ ሲደርሱም ምርኮኛዋ ራሳቸውን ለማጥፋት አካላቸውን ቀደው ወደ ሰውነታቸው መርዝ ሲጨምሩ አገኝዋቸው። ካሣ እኚህን ምርኮኛ እስከዚያች ቀን ድረስ በዓይናቸው አይተዋቸው አያውቁም ነበርና በውበታቸው በእጅጉ እየተደነቁ በአካላቸው ላይ የጨመሩት መርዝ ወደ ሌላው የሰውነት ክፍላቸው እንዳይዛመት ከወደቁበት በፍጥነት አጎንብሰው ከተቀደደው የሰውነት ክፍላቸው ላይ መርዙን በአፋቸው እየመጠጡ ያወጡላቸው ጀመር። ካሣ ይህን ፈፅመው ሲያበቁ ምርኮኛዋ ለሞት የሚያሰጋቸው ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውን አረጋግጠው እንደገና በፍጹም ጀግንነት ያሉበትን የጠላት ቀጠና ለቀው በመውጣት ለወላጆቻቸው አስረከቡ። ካሣ በዚህ ሁኔታ ከምርኮ ያስለቀቋቸውና ከሞት ያተረፏቸው ሰው በኋላ ተወዳጅ ሚስታቸው የነበሩት ተዋበች ዓሊ ነበሩ።

ተዋበች ዓሊ የመስፍኑ የራስ ዓሊ ልጅ እንዲሁም የንግሥቲቱ የእቴጌ መነን የልጅ ልጅ ናቸው። ካሣ በሽፍትነት ዘመናቸው በሱዳን ወሰን በኩል የሚቃጣውን የአረቦችን ጥቃት በተደጋጋሚ በድል በመመለሳቸው ዝናቸው እየናኘ ሄዶ ነበር። ታድያ ይህን የተገነዘቡትና በጎንደር የተቀመጡት ንግሥቲቱ እቴጌ መነን ካሣን የመሰለ ጀግናን በጠላትነት ፈርጆ ጦርነት ከመግጠም ይልቅ በወዳጅነት መያዙ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አምነው ወይዘሮ ተዋበች ዓሊን በመስጠት በጋብቻ እንዲተሳሰሩ አደረጉ።

ምንም እንኳን ጋብቻው እንደታለመው የወዳጅነት አለመሆኑን የሚያስረዱ ሁኔታዎች ብዙህም ሳይቆይ ቢታዩም የተዋበች ዓሊና የመይሳው ካሣ አስደናቂ ፍቅርና የህይወት ትስስር ግን እስከ መቃብር ድረስ የፀና ነበር። ለዚህም ካሣ ገዳሪፍ ላይ ከቱርክ ጦር ጋራ ተዋግተው ድል ካደረጉ በኋላ ቆስለው ስለነበር ለማገገም በደንቢያ ተኝተው እንዳሉ ማገገሚያ የሚሆን ስንቅ ስላጠራቸው እንዲላክላቸው ወደ አማቾቻቸው መልዕክት ቢሰዱ እቴጌ መነን ካሣን ንቀው አንድ ብልት ስጋ ከስድብ ጋር በመላካቸው ተዋቡ ተበሳጭተውና እጅግ ተቆጥተው” ደፋሮችን እወዳለሁ። ፈሪዎችን ግን እንቃለሁ።” በማለት ጥቃታቸውን ለመከላከልና በደላቸውን ለመሻር ካሣን አነሳስተው የወደፊት ራዕያቸው ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን።

መቼም ሰው ሲሆኑ መሳሳት፣ ሲያፈቅሩ መጠራጠር አይቀርምና ካሣ በዘመነ መሳፍንት የተበታተነችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ላይ ታች በሚኳትኑበትና ውጊያ የዕለት ተዕለት መደበኛ ተግባራቸው ሆኖ በነበረበት ግዜ ቤተሰባቸውን ከጥቃት ለመከላከል በማሰብ ሚስታቸውን ወይዘሮ ተዋበች ዓሊን ከአደጋ ለማሸሽ አይከል ኮልባ ከተባለ ታማኝ ወዳጃቸው ዘንዳ ወሬ ሳይሰማ በዋሻ ውስጥ እንዲቀመጡ አድርገው ነበር ። ይህን ባደረጉ ከቀናት በኋላም ከዕለታት ባንዱ ዕለት ካሣ አንዱን አሽከራቸውን ጠርተው ስለ ወይዘሮ ተዋበች ጤንነት ቢጠይቁ “እሳቸውማ ምን አለባቸው የአይከል ኮልባን ልጅ ዘውዴ አይከልን ወዳጅነት ይዘው ይሽሞነሞናሉ እንጂ!” ብሎ ቢነግራቸው ካሣ እንኳን ለራሳቸው ለሌላውም የሚቀኑ ሰው ነበሩና ወዲያው ለአይከል ኮልባ ወይዘሮ ተዋበች ዓሊን አሉበት ድረስ ይዘው እንዲመጡ መልዕክት ላኩባቸው። እንደመጡም ካሣ በቁጣ ተንጠው በእልህ ተውጠው ወይዘሮ ተዋበች የተጠረጠሩበትን ክስ ቢመረምሩ ከታማኝነታቸው ውጪ አንዳች አይነት ክህደት ከሚስታቸው ዘንዳ ለማግኘት ባለመቻላቸው የተነገራቸው ውሸት መሆኑን አወቁ። ማተባቸውን አጥባቂ ቃልኪዳናቸውን ጠባቂ የሆኑትን ተወዳጅ ሚስታቸውን ወይዘሮ ተዋበች ዓሊን በአንድ አሾክሻኪ አሽከር ተራ ያሉባልታ ወሬ የተነሳ በመጠርጠራቸውም ካሣ ፀፀት ተሰምቷቸው ነበር።

ተዋበች ዓሊ ለሀገር አንድነት አንድም ቀን በመንፈስ ያልደከሙ ብርቱ ሰው ነበሩ። በተንጣለለ አዳራሽ ጠጅ ከገንቦኛ እያስቀዱ ከማንቆርቆር ስጋ ከመልከኛ እያስቆረጡ በድሎት ከመኖር ይልቅ ለአላማቸው ፅናት ዋሻን የሚመርጡ ጀግና ሴት ነበሩ። በቆላ ሀሩርና በበርሃ ንዳድ እየተንከራተቱ የቴዎድሮስን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ከልባቸው ባላቸውን የሚደግፉ ሁነኛ አጋር ነበሩ። ለሀገር አንድነት ጠንቅ የነበረውን የዘመነ መሳፍንትን አገዛዝ ለመቃወም የስጋ ዝምድና እንኳን ያልበገራቸው በአባትና አያታቸው ጭምር የጨከኑ ቆራጥ ሴት ነበሩ። ምንም እንኳ የአላማቸው ፅናት እንዲህ ያለ ሆኖ ቢገኝም አባታቸው ራስ ዓሊ ከካሣ ሸሽተው በበርሃ ዋሻ ተደብቀው በነበረ ግዜ ክፉኛ መቸገራቸውን በመስማታቸው አንጀታቸው አልችል ብሎ በድብቅ ምግብና ልብስ ይልኩላቸው ነበር።

ተዋበች ዓሊ ለመይሳው ካሣ ተወዳጅ ሚስት ብቻ አልነበሩም። አማካሪም አስተማሪም እንጂ። ተዋበች በሞቱ ግዜ ካሣ:-

“እስቲ ጠይቁልኝ ርቃ ሳትሄድ

እቴጌ ተዋበች ሚስትናት ገረድ” በማለት የተቀኙላቸውም ለዚሁ ነበር። ምንም እንኳን ካሣ ለሀገር አንድነት በነብራቸው ፅኑ ዓላማ ምህረት የለሽ ርምጃዎችን የሚወስዱ እና ቆራጥ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፉ መሪ ቢሆኑም ይልቁንም በስልጣናቸውና በሀይላቸው ተገፋፍተው ሰብዓዊ ሚዛናቸው እንዳይዛነፍ እቴጌ ተዋበች ተወዳጅነታቸውን በመጠቀም ዕለት በዕለት እየተከታተሏቸው ምክር ይለግሷቸው ነበር። ትግሳፅና ቁጣ ያሰሟቸው ነበር። በዚህም ካሣ ፈሪሃ እግዚአብሔር በልባቸው እንዲያድር ተዋበች የቅዱሳን መፃህፍትን ጭምር ያነቡላቸውም ነበር። ከእቴጌ ተዋበች ሞት በኋላ ግን ካሣ ተለዋዋጭ ባህሪ እስከማፍራትና የሰብዓዊነት ሚዛናቸውን የሳቱ አደገኛ ውሳኔዎችን እስከመወሰን የደረሱበት ሁኔታ በስፋት ተፈጥሮ ነበር።

አፄ ቴዎድሮስ ሸዋ ዘምተው ድል በማድረግ ሸዋን በግዛት አንድነት ውስጥ ከጠቀለሉ በኋላ ወደ ጎንደር ተመልሰው ጥቂት እረፍትን ብቻ በዚያ አድርገው ሲያበቁ እንደገና የሸፈተባቸውን የወሎን ባላባት ለማስገበር ሚስታቸውን እቴጌ ተዋበችን ይዘው ወደ ወሎ ጉዞ ጀምረው በጉዞ ላይ እንዳሉ አርብ ገበያ ከተባለ ስፍራ ላይ ሲደርሱ እቴጌይቱ በጠና በመታመማቸው ምክንያት በአልጋ ላይ ሆነው ጉዞ ለማድረግ ተገደው ነበር። ከዚያም ህመማቸው ይበልጥ ተባብሶ ነሐሴ 13 ቀን 1850 ዓ.ም ግራኝ ሜዳ ከተባለ ስፍራ ላይ ሞቱ። እቴጌ ተዋበች ከታመሙበት ዕለት አንስቶ ሽምብራ ብቻ እየቆረጠሙ ፆም ፀሎት እያደረጉ የቆዩት አፄ ቴዎድሮስም መሪር ሀዘን ላይ ወደቁ። እረፍት አሳጥተዋቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው ጋራ እየታገሉም ግሼን አስወጥተው ቀብራቸውን አስፈፀሙ።

ራስ ዓሊ ከካሣ ሸሽተው በበርሃ ዋሻ ተደብቀው ሳለ በፅኑ መቸገራቸውን የሰማችው ልጃቸው ተዋበች በድብቅ ትረዳቸው ሰለነበር ሞትዋን በሰሙ ግዜም በእጅጉ አዝነው፡-

“ጠጅ አማረኝ ስላት ማሩን ታስጭናለች

ራበኝም ስላት እህል ትልካለች

በረደኝም ስላት ሸማ ትሰዳለች

ሌባዬ ተይዛ ባልጋ ትሄዳለች።” በማለት በገና እየደረደሩ አለቀሱ።

አፄ ቴዎድሮስም ከተወዳጅ ሚስታቸው ከእቴጌ ተዋበች ሞት በኋላ የባህሪ ለውጥ አስከትለው እንደነበረ ይነገራል። ተዋበችን የሚያስታውሳቸው አጋጣሚ የተፈጠረ እንደሆነ ትዝታቸው ተቀስቅሶ እንባቸውን መቆጣጠር ያቅታቸው እንደነበርም ይወሳል። እንዲያውም አንድ ወቅት ላይ አንድ ብረት ቀጥቃጭ የሆነ የንጉሡ አገልጋይ ከቴዎድሮስ ፊት ቀርቦ ሚስቱ በጠና መታመምዋን በመግለፅ እርሷን ለማስታመም የሚሆን ፍቃድ እንዲሰጠው ቢጠይቅ አፄ ቴዎድሮስ በሰራተኛቸው ጥያቄ ልባችው ተነክቶ ወዲህም የሚስታቸው የእቴጌ ተዋበች ሀዘን ተቀስቅሶ ራሳቸውን ወደ መሬት አቀርቅረው ማልቀሳቸውም ይነገራል።

በቸር ያቆየን!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...