በእነ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን የሚያቋቁመው አዲሱን ፖርቲ ለማቋቋም ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንት ጊዚያዊ ዕውቅና እንደሚሰጠው ተገልጿል፡፡
ፓርቲውን ለማቋቋም ሕገ ደንብና ፕሮግራም ተቀርፆ ያለቀለት መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት፤ አቶ ጣዕመ አርዓዶም ናቸው፡፡
አቶ ጣዕመ ከዚህ በፊት የህወሓት አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ህወሓት ቡድን አባል መሆናቸውንና አዲስ ለሚቋቋመው ፓርቲ ጭምር አባል መሆናቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲውን ለማቋቋም አስፈላጊው መስፈርት ተሞልቶ ለምርጫ ቦርድ እንደገባ የሚናገሩት አቶ ጣዕመ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፓርቲው ሕጋዊ ፍቃድ እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ፓርቲው ጊዚያዊ ዕውቅና እንደጠየቀ የገለጹ ሲሆን፤ “ይህም አዲስ የሚቋቋመው ፓርቲ በሦስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጎ ሙሉ ዕውቅና እንዲያገኝ ያስችለዋል” ብለዋል፡፡
አሐዱም “ከፓርቲው አዲስ ስያሜ ጋር በተገናኘ እየተገለጸ ያለው የትግራይ ሊብራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የሚለው ስያሜ ትክክል ነው ወይ?” ሲል ጠይቋል፡፡
አቶ ጣዕመ በሰጡት ምላሽም፤ ፓርቲው ሊብራል ዲሞክራሲ መሆኑን በመግለጽ ነገር ግን ከስያሜው ጋር በተገነናኘ የሚነሳው ሀሳብ ትክክል አለመሆኑና ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ከስያሜው ጋር በተያያዘ በርካታ ሀሳቦች ሲነሱ መቆየታቸውን የገለጹም ሲሆን፤ “ፓርቲው ሊብራል ዲሞክራሲ ሆኖ አጠቀላይ ሊብራል ፓርቲ ቢሆንም የትግራይ ማህበራዊ እሴትን የተከተለ ለማድረግ ተሰርቷል” ብለዋል፡፡
ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ በርካታ ውዝግብ ከተፈጠረበት ወዲህ በተለይም በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህዋሓት ቡድን አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁም መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ለመሆኑ “የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የፈረሙት የድርጅቱ አባል እና ከፍተኛ አመራር ከህወሓት ወጥተው አዲስ ፓርቲ የሚያቋቁሙ ከሆነ ይህ ስምምነት ባለቤትነቱ የማን ይሆን?” ሲል አሐዱ ጠይቋል፡፡
አቶ ጣዕመ ይህንን ሲመልሱም “የስምምነቱ ዋና ባለቤት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው” ብለዋል፡፡
አዲስ የሚቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ የህወሓት መሰረዝን ተከትሎ፣ በክልሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፓርቲ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህ ፓርቲ ለቀጣይ ምርጫም ክልሉን ወክሎ ይወዳደራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
