የኢትዮጵያ ፖስታ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 3 ሺሕ በሚጠጉ ቅርንጫፎቹ በኩል የባንክ አገልግሎቶችን / Agency Banking ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
አሰራሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የንግድ ባንኮች በጋራ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩትን “ኢቲ-ስዊች” የክፍያ መረብ መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ700 ቅርንጫፎች በሙከራ ደረጃ ሥራ መጀመሩና በወር ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።
በዚህም ደንበኞች የትኛውም የባንክ ሂሳብ ቢኖራቸው በፖስታ ቤት መስኮቶች በኩል ገንዘብ ገቢና ወጪ ማድረግ፣ የፍጆታ ክፍያዎችን መፈጸም እና የባንክ ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ ያስችላቸዋል።
በሌላ በኩል፣ ባንኮች ወጪ ለመቀነስ ሲሉ ቅርንጫፎቻቸውን በሚዘጉበት ወቅት የኢትዮ ፖስት ወደ አገልግሎቱ መግባት የተለያዩ አስተያየቶች እንዲነሱ አድርጓል።
አንዳንዶች የባንክ አገልግሎት ወደ ተንቀሳቃሽ ሞባይል በሰፊው እየተቀየረ ባለበት ወቅት ቅርንጫፎችን መሠረት ያደረገ አሰራር ውጤታማነቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ሲገልጹ፤ ሌሎች ደግሞ አሰራሩ ባንኮች ባነሰ ወጪ ተዳራሽነታቸውን እንዲያሰፉ ይረዳል ሲሉ ያነሳሉ።
አዲስ ፎርቹን
