ለእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 500ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ በማለት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
የዘንድሮ መውሊድ በሁለት ታላላቅ ክስተቶች መሐል የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያለው ተቋሙ፤ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤቱ ድርጅታዊ መዋቅር ምርጫ ተከናውኖ ወደ መቋጫው በደረሰበት ወቅት መከበሩ ነው ብሏል፡፡
ሌላው ደግሞ የአንድነታችን ምሰሶና የሕብረታችን ማሳያ፣ የጥረት፣ የጽናት እና የትብብር ምሳሌና ምልክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ የምረቃ ጊዜውን በጉጉት በምንጠባበቅበት ሰሞን መከበሩ ነው ሲል ገልጿል።
የ1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል ሲከበር በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህል ሊሆን እንደሚገባ እንዲሁም በሕመም አልጋ ላይ እና በሕግ ጥላ ስር የሚገኙትን ወገኖቻችንን በመጠየቅ እና በማበረታታት፣ በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙት ወገኖቻችን በዓሉን በደስታ ማክበር ይችሉ ዘንድ ያለንን በማካፈል መሆን አለበት ሲል አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
በዓሉ ሲከበር ለሀገራችን ሰላም፣ ለሕዝባችን አንድነት እና በረከት ከልብ የሆነ ዱዓ በማድረግ መሆን አለበት ነው ያለዉ።
