በኣጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኣጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት በሙሉ!
ፍጥረቱን በትክክለኛ መርሕ የሚያስተዳድር እግዚአብሔር ኣምላክ ከኣራቱ መዓዝነ ዓለም ኣሰባስቦ በዚህ ቅዱስና ሓዋርያዊ ጉባኤ ስለ ሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእሱ ይሁን፤ እናንተም ወደ ቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ ጉባኤ እንኳን በደኅና መጣችሁ!
“ኲሉ ማዕምቅ ይምላእ፣ ወኲሉ ወግር ይተሓት ወኲሉ መብእስ ይኩን መጽያሕተ ርቱዐ፤ ወይርኣይ ኲሉ ዘነፍስ ኣድኅኖቶ ለእግዚአብሔር፡- ዓዘቅቱ ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፤ ሸካራውም ይስተካከል፤ ሥጋዊም ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ (ሉቃ. 3፥6)
የዚህ ትምህርተ መለኮት መሠረታዊ መልእክት ትክክለኛ፣ ፍትሕንና እኩነልነትን በማኅበረ ሰብ መካከል ማረጋግጥ ነው፤
ፍትሕና እኩልነት ለሰው ልጅ ያላቸው ዋጋ፣ ከምግብ፣ ከመጠጥና ከልብስ ፍላጎት ያልተናነሰ ነው፤ የሰው ልጅ ደስታና የኅሊና ነጻነት የሚለካው ኣስተማማኝ በሆነ የፍትሕና የእኩነልነት ሃልዎት እንጂ በምግብ፣ በመጠጥና በልብስ ወይም በሃብት ብዛት አይደለም፤ ብዙ ሃብት ያላቸው ሰዎች ፍትሕንና እኩልነትን ካጡ፣ ኅሊናዊ ተሃውኮ ላይ ይወድቃሉ፤ ኑሮኣቸውም በእጅጉ ይረበሻል፤ ለሃብታቸውም ዋስትና እንደሌለው ስለሚረዱ ነገራቸው ሁሉ ይቃወሳል፣ ይናጋልም፡፡
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት!
የተከበራችሁ እንግዶች!
ፍትሕና ርትዕ ለሰው ልጅ የተቃና ኑሮ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጡ ምርጥ ስጦታዎች ናቸው፤ ፍትሕና እኩልነት በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር ሲውሉ ለሰው ኅሊና ፍጹም ነጻነትን ያጐናጽፋሉ፤ ሲዘነጉና ሲናቁ ግን ኑሮው የተመሰቃቀለና ተስፋ ቢስ የሆነ ማኅበረ ሰብ ይፈጠራል፤ ነገሩ ሲራዘም ደግሞ ግጭትን ይወልድና መጠፋፋትን ያስከትላል፤ ፍትሕና እኩነልነት የእግዚአብሔር ገንዘቦች እንደመሆናቸው መጠበቅና መከበር ያለባቸው በቤተ እግዚአብሔር ነው፤ “ፍትሑ ለነዳይ ወለዕጓለ ማውታ ወኣጽድቁ ግፉዐ ወምስኪነ” የሚለውን ትምህርት የምናገኘው በቤተ እግዚአብሔር ነውና፤
ይሁን እንጂ “በኣንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” እያልን ኣንዱ ደብር የተራራ ያህል በሃብት የናጠ፣ ሌላኛው ደብር ደግሞ ሁሉን ኣጥቶ የተዘጋ ነው፤
በሰው ኃይል ኣስተዳደርም ኣንዱ ከበቂ በላይ ደመወዝ ሲያገኝ፣ ሌላው ድቃቂ ሳንቲም ኣጥቶ በችግር ይማቅቃል፤ በኣድልዎ፣ በጥቅም ትስስርና በብልሹ የሃብት ኣያያዝ የሚከሠተው ምዝበራ ሁሉ የፍትሕና የእኩልነት እጦት ውጤት ነው፤
እንደዚህ ዓይነቱ ብልሹ ኣሰራርን ካላረምን በቀር መልካም ኣስተዳደርን ማስፈንና ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የማንወጣው ከባድ ዳገት ይሆንብናል፡፡
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት
የተከበራችሁ እንግዶች!
የሰው ኃይል ኣስተዳደራችን ፈተና የበዛበት፣ ከፍ ያለው ዝቅ ይበል፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይበል፤ የተጣመመው ቀጥ ይበል፤ ሰው ሁሉ የራሱን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ይመልከት ያለውን መለኮታዊ ኣስተምህሮ ወደ ጐን ስለ ተተወ ነው፤ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችንና ልጆችዋ ካህናት እየተጐዱብን ነው፤ ለዚህም ያለ በቂ ምክንያት ከስራና ደመወዝ እየተፈናቀሉ እሮሮ የሚያሰሙ ካህናትና ሰራተኞች በርካታ ናቸው፡፡
ቀደም ሲል በተፈጸመው የማፈናቀል ክሥተት ከተጐዱ ካህናት መካከልም እስካሁን ዕንባቸው ያልታበሰ ብዙ ናቸው፤ ችግሩም ሲቆም አይታይም፤ በየጊዜው ባለሥልጣን ይነሣል፤ ባለሥልጣን ይተካል፤ ችግሩ ግን ከመባባስ በቀር ምንም ዓይነት መሻሻል ኣይታይበትም፤ ለምን እንደዚህ ሆነ ብለን ብንጠይቅ፣ ችግሩ የቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፣ እኛው ራሳችን ፍትሕንና እኩልነትን ለማስፈን ቊርጠኝነቱን ስላጣን ነው የሚል መልስ ያመዝናል፤ ከዚህ ሌላ ምንም ዓይነት ኣመክንዮ ሊቀርብለት ኣይችልም፤
ስለሆነም ይህ ጉባኤ የችግሩን ኣሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት ፍትሕንና እኩልነትን፣ ሥርዓትንና የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አሰራር የሚያዋልድ ኣቅጣጫ መቀየስ ይኖርበታል፤ ወጣ ገባውና ኣንዱ በይ ሌላው የበይ ተመልካች የሚያደርገውን እንደዚሁም ሐዋርያዊ ተልእኮን ያላስቀደመ ልማዳዊ ኣሰራር ማረም አለብን፤ በምትኩም በቴክኖሎጂ ሲስተም የታገዘና ሁሉንም በፍትሕ ፊት እኩል ኣድርጎ የሚያስተናግድ ኣሰራር በዚህ ዓመት ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ ስለሆነም ይህ ጉባኤ ለዚህ ትክክለኛና ችግር ፈቺ ውሳኔ እንዲሰጥበት በኣጽንዖት እናሳስባለን፡፡
በመጨረሻም
ከኣራቱ መዓዝነ ዓለም የመጣችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ኃላፊዎችና ተጠሪዎች የዘመኑን ፈተና ተቋቊማችሁ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝቡን በቅንነት ከማገልገላችሁም በላይ፣ ደጋ ወጥታችሁ፣ ቆላ ወርዳችሁ ያስገኛሁትን ውጤት በመያዝ በዚህ ጉባኤ መገኘታችሁን በኣድናቆት የምንመለከተውና ምስጋና የምንቸረው መሆኑን እየገለጽን እንኳን ደኅና መጣችሁ በማለት የሁለት ሺሕ ዓሥራ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተከፈተ መሆኑን እናበስራለን፡፡
እግዚአብሔር መልካም ጉባኤ ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘኣኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ጥቅምት 3 ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
