የሽብር ተከሳሹ ካናዳዊው እሱባለው በለጠ ከአንድ ዓመት እስር በኋላ በነጻ ተሰናበተ

Date:

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ዜግነት ያለው እሱባለው በለጠ በነጻ ተሰናብቶ ከእስር መፈታቱን ለቢቢሲ ተናገረ።

ከመስከረም 24/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ የቆየው እሱባለው፣ መስከረም 28/2019 ዓ.ም መለቀቁን ገልጿል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በነጻ እንዲለቀቅ ውሳኔ በሰጠበት እለት ነው ከእስር የተለቀቀው።

ሦስቱም የችሎቱ ዳኞች በነጻ እንዲሰናበት በሙሉ ድምፅ ውሳኔ መስጠታቸውን እሱባለው ለቢቢሲ አስረድቷል።

ካናዳዊው እሱባለው በለጠ ብርሃኔ፣ በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ለተከሰሱ እስረኞች የቀረበውን በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ “ይቅርታ መጠየቂያ ሰነድ” ለመፈረም ፈቃደኛ ካልሆኑ 30 ተጠርጣሪዎች አንዱ ነው።

እሱባለው፣ የወላጅ እናቱን ህልፈተ-ሕይወት ተከትሎ ለለቅሶ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ፣ መስከረም 24/2018 ዓ.ም ወደ ካናዳ ለመመለስ አውሮፕላን ሊሳፈር ሲል ከቦሌ አየር ማረፊያ ነበር በፀጥታ ኃይሎች የተያዘው።

ተጠርጥሮ የተከሰሰበት የሽብር ወንጀል፣ በውጭ ካሉ የፋኖ ደጋፊዎች ጋር በመተባበር፣ በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሰው “ታጣቂ ኃይል የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ” እንደነበር ጠበቃው እና ተከሳሹ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር የተያያዙ አራት ክሶች ቀርበውበት እንደነበር የገለፀው እሱባለው፣ መከላከያ ካቀረበ በኋላ በነበሩ አምስት ቀጠሮዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ በፍርድ ቤቱ መገለፁን አስረድቷል።

“ዐቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ በተሰጠው ዕድል ያለውን ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጾ ነው ፍርድ ቤቱ በነጻ እንድሰናበት ውሳኔ የሰጠው” ሲል ተናግሯል።

“በቁጥጥር ስር የዋልኩት በሀሰተኛ ጥቆማ ነበር” የሚለው እሱባለው፣ ጉዳዩ እልባት ማግኘቱ ቢያስደስተውም “መጓተቱ” ግን “ሕይወቴን አመሰቃቅሎታል” ይላል።

በካናዳ የቶሮንቶ ፒርሰን አየር ማረፊያ “ከፍተኛ የአውሮፕላን ጥገና ባለሞያ (ግራውንድ ቴክኒሺያን)” ሆኖ ሲሠራ የነበረው እሱባለው በለጠ፣ በእስር ላይ በነበረበት ጊዜ ሥራውን ማጣቱን ተናግሯል። “አየር መንገዱ በእስር ላይ መሆኔን ተረድቶ ከ10 ወራት በላይ ከጠበቀኝ በኋላ፣ አሰናብቶኝ በቦታው ሌላ ሰራተኛ ቀጥሯል” ብሏል።

በተጨማሪም “ክሬዲት ካርዴ ሙሉ በሙሉ ተበላሽቷል። የመኪና ኢንሹራንስ መክፈል ስላልቻልኩ ተዘግቷል፤ አንዴ ክሬዲት ካርድ ከተበላሸ እንደ ቤት ያሉ ከፍ ያሉ ነገሮችን ለመግዛት 7 ዓመት መጠበቅ አለብኝ። ተከራይቼ የምኖርበት ቤት ማስታወቂያ አውጥቶ መልስ የሚሰጠው ስላጣ እቃዬን በሙሉ አውጥቶ ለሌላ አከራይቷል” ሲልም የገጠመውን ሁኔታ አብራርቷል።

እናም ወደ ካናዳ በሚመለስበት ወቅት ህይወትን “ከዜሮ ለመጀመር” እንደሚገደድ በመጥቀስ፣ “የፍትህ ስርዓቱ መጓተቱ ቅሬታ አሳድሮብኛል” ሲል ገልጿል።

እሱባለው ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ ካናዳ ለመመለስ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች እያጠናቀቀ መሆኑን ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም ለቢቢሲ አስረድቷል። የቀረበበትን ክስ በሚከታተልበት ወቅት የካናዳ ኤምባሲ ባለሞያዎችን በመመደብ የማማከር አገልግሎት ሲሰጠው እንደነበረም ገልጿል።

BBC

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ እና የቻይና አየር መንገዶች የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቻይና ሳውዘርን አየር መንገድ በቻይና...

ሁቲዎች በሳዑዲ የነዳጅ ኩባንያ አስተዳደር ሕንጻ ላይ በፈጸሙት ጥቃት በእሳት ተያያዘ

የሳዑዲ አረቢያ የኢነርጂ ሚኒስቴር በአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት የሚገኘው ከዓለም...

የሹመት ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ሹመት የሰጧቸው አመራሮች፡- 1. አቶ...

እንደዚህ ዓይነቱ ብልሹ ኣሰራርን ካላረምን በቀር መልካም ኣስተዳደርን …

በኣጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኣጠቃላይ...