በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለሥራ ፈጣሪዎች የ16 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን የኦሮሚያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ካሣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኢንተርፕርነርሺፕ ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን ለሥራ ፈጣሪዎች 16 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረብ የተቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብድር ወስዶ ወደ ሥራ ከመግባት አንጻር ማኅበረሰቡ ፍራቻ እንደነበረበት አንስተው፤ ይህም በ2016 በጀት ዓመት የቀረበው ብድር 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠናው ለአርሶ አደሩ በዘመናዊ መልክ የግብርና ሥራን መሥራት የሚያስችል፤ በአምራች ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ምርታቸውን ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጭ የሚያቀርቡበትን እና በስፋት ተኪ ምርት ማምረት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማስቻል ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተሰጠው ሥልጠና እና የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ በኋላ ወደ ሥራ መግባት እንዲችሉ የብድር አገልግሎት ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል፡፡
የተሰጡ ሥልጠናዎች ውጤታማ በመሆናቸው በ2017 በጀት ዓመት በ182 ሺህ ኢንተርፕራይዝ፤ ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተደራጅተው ወደ ሥራ መሰማራታቸውን ተገልጿል ።
NBC Ethiopia
