ኢራን እና አይሁድ ምንና ምን ናቸው?
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
- እንደ መንደርደሪያ፤
ግዮን መጽሔት :- በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከ72ቱ አርድዕት መካከል የሚመደበው ወንጌላዊው ሉቃስ- በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዘንድ፤ ‹‹ባለመድኃኒቱ/ሐኪሙ እና የታሪክ አዋቂው›› ቅዱስ ሉቃስ በስሙ የተመዘገበለትን የሉቃስ ወንጌልን እና ግብረሐዋርያትን (የሐዋርያት ሥራ) መጻሕፍትን እንደጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ያረጋግጡልናል፡፡
ወንጌላዊው እና ታሪክ አዋቂው ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር እንዲህ በሚል ኃይለ-ቃል ነው የሚጀምረው፤
‹‹የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች “ታሪክን” በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ “በጥንቃቄ” ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤››
(የሉቃስ ወንጌል ፩፤:፩-፬)።
- የአይሁዳውያኑ ጠበቃ ኢራን/ፋርስ!!
ስመጥር ፈላስፋ እና የሂፖው ሊቀ ጳጳስ የነበረው አውግስጢኖስ፤ ‹‹ታሪክ በቀላሉ ያለፈው ዘመን አይደለም፤ በጊዜ ውስጥ የተጻፈ የመለኮታዊ ዕቅድ አካል/ታሪክ ነው፤›› ይለናል፡፡
በርግጥም የሰው ልጅ፤ የዓለም ታሪክ ከአምላክ/ከመለኮታዊው ዕቅድ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት አለው፡፡ ይህን እውነታ በደንብ ለመፈተሽ ያግዘን ዘንድም ሰሞኑን አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጥቃት መነሻ አድርገን ወደኋላ ተጉዘን ታሪክን ለመፈተሽ እንሞክር፤
ከሰሞኑን አሜሪካና እስራኤል በጋራ በኢራን ላይ የተከፈቱት መጠነ ሰፊ ጥቃት የዓለማችን ትልቅ ዜና፤ በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ የ3ኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ይሆን እንዴ?! በማለት እያንዳንዱን ክስተት በጥንቃቄ እየተከታተሉት ይገኛሉ፡፡
በነገራችን ላይ አሜሪካና እስራኤል በጥንታዊቷ አገር ኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት እንዲህ ሲሉ ነው የገለጹት፤
‹‹The goal of these strikes is to remove the existential threat posed by the terrorist regime in Iran.››
የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚ/ር ደግሞ፤
The strikes were ‹‹a pre-planned and unprovoked act of armed aggression against a sovereign state.›› በማለት የእነ እስራኤል ጥቃት የዓለም አቀፉን ሕግ የጣሰ ጦርነት መሆኑ በማስረገጥ አምርረው ኮንነውታል፡፡
‹‹እስራኤል ከምድረ-ገጽ፤ ከካርታ ላይ መፋቅ አለባት፤›› የምትለው ኢራን የዛሬን አያድርገውና በጥንቱ ዘመን የአይሁዳውያኑ ጠበቃ ነበረች፡፡ የዛሬዋ ኢራን/ፋርስ በአምላክ መለኮታዊ ዕቅድ መሠረት አይሁዳውያንን ከባቢሎን መንግሥት ባርነትና ግዞት ነጻ መውጣት ምክንያት የሆነች የታላቅ ሥልጣኔ እና የገናና ታሪክ ባለቤት ናት፡፡
እንዴት የሚለውን በደንብ ለማየት ያስችለን ዘንድ ከቅዱስ መጽሐፍ በማጣቀስ አሁንም አብረን እንዝለቅ፡፡
እስራኤላውያን በበደላቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት የአባቶቻቸውን አምላክ በማሳዘናቸው የተነሳ ከምድራቸው ተግዘው በባቢሎን ምድር ለ70 ዓመታት በባርነት ቆይተዋል፡፡ መጽሐፍ እንዲልም፤
‹‹እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ፡፡
ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ፡፡
ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ፡፡
አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ፡፡
ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል፤›› እንዲል፡፡
(ሚክያስ ምዕ. ፫፥፰-፲፪)
አይሁዳውያኑ በጦርነት ሞተው፤ ጎበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ወድቀው፤ ደናግላውያኑ በሃፍረት አንገታቸውን በአደባባይ ደፍተው… እንደ ነፍሳቸው የሚሳሱለትም ቤተ-መቅደሳቸው ፈርሶ፤ በሕይወት የተረፉት በምርኮ ወደ ባቢሎን ምድር ተግዘው ነበር፡፡
አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ ይህን የሕዝቡን ሰቆቃ፣ ምሬትና ታላቅ መከራ ሰቆቃወ ኤርምያስ በሚለው መጽሐፉ ከከተበው ጥቂት ኃይለ-ቃላትን እንቀጭብ፤
‹‹እስራኤል አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የእናቶች ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ ደናግላን ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ፡፡
ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፤ እርስዋም በታላቅ ምሬት ውስጥ አለች፡፡
ሴቶችን፥ በከተሞቿም ደናግልን አጐሰቈሉ፤ አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ በመቅደሱ የካህናት፣ በአደባባይም የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም፡፡
ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ፡፡ ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ። አቤቱ፥ ተጨንቅናል፥ አንጀታችም ታውኮብናልና፤ ተመልከት ልባችን በውስጣችን ተገላበጠብን፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቻችንን አጠፋ፤ በቤታችንም ሞት አለ፡፡
ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን፡፡ ስለ ወገናችን ሴት ልጆች ቅጥቃጤ ዓይኖቼ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኖቼ ሳያቋርጥ ዝም ሳይሉ እንባን ያፈሳሉ፡፡
የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል፤ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኖቼ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ፡፡
እስራኤል ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው?! ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል፡፡
አቤቱ የሆነብንን አስብ…!!›› (ሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ)
- ማኔል፣ ተቄል ፋሬስ
የዳንኤል መጽሐፍ እንደሚተርከው፤ ንጉሥ ናቡከደነፆር እስራኤልን ወደ ባቢሎን ምድር ባጋዛቸው ጊዜ ከአይሁዳውያኑ ቤተ-መቅደስ የዘረፋቸውን ንዋያተ ቅድሳት አውጥቶ ባዘጋጀው ድግስ ላይ መጠቀሚያ አደረጋቸው፡፡ ከአባቱ ናቡከደነፆር ትዕቢትና የድፍረት ኃጢአት ያልተማረው ብልጣሶር እርሱም በአባቱ የትዕቢት መንገድ ተጉዞ የእስራኤል አምላክን አሳዘነ፡፡ የቤተ-መቅደሱን ንዋይተ ቅድሳት አስመጥቶ ከመኳንንቱና ከዕቁባቶቹ ጋር መጠጫና መደሰቻ አደረጋቸው፡፡
ንጉሡ ብልጣሶር፣ ባለሟሎቹና ዕቁባቶቹ ጣራ በነካ ደስታ ፌሽታ ውስጥ እንዳሉ አንዲት እጅ በቤተመንግሥቱ የግብር ቤት የግድግዳ ላይ እንዲህ ሲል ጻፈች፤
ማኔል፤ ተቄል፤ ፋሬስ!!
ያ በደስታና በፌሽታ የተጥለቀለቀ የንጉሡ የግብር አዳራሽ በድንገት በድንጋጤ ማዕበል ተመታ፤ በግብዣው ላይ የታደሙ ሁሉ ልባቸው ቀጥ አለ፤ የንጉሡ ፊትም በድንጋጤና በፍርሃት ዐመድ ለበሰ፤ የመጽሐፈ ዳንኤል ጸሐፊ፤ ‹‹… ከጽሕፈቲቱ የተነሳ የንጉሡ ብልጣሶር የወገቡ ጅማት ተፈታ፤›› ሲል የድንጋጤውን መጠን ምን ያህል ታላቅና ከባድ እንደነበር ሊገልጸው ሞክሯል፡፡
ንጉሡ የጽሕፈቱን ምስጢር እንዲፈቱለት የመንግሥቱን ጠቢባንና አዋቂዎች ቢያማክርም አንዳቸውም ምስጢሩን ሊፈቱት አልተቻላቸውም ነበር። እናም በንጉሡ የቅርብ ባለሟሎች ዘንድ የሚታወቀው አይሁዳዊው ምርኮኛ፤ ምስጢርን ይፈታ ዘንድ መለኮታዊ ጥበብ የተሰጠው የእግዚአብሔር ሰው ዳንኤል ወደ ንጉሡ የግብር አዳራሽ በክብር ተጠራ፡፡
ንጉሥ ብልጣሶርም ለዳንኤል እንዲህ አለው፤
‹‹… የአማልክት መንፈስ እንዳለብህ፥ እውቀትና ማስተዋልም መልካምም ጥበብ እንደ ተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ፡፡ አሁንም ይህን ጽሕፈት ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ያስታውቁኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች ወደ እኔ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የነገሩን ፍቺ ያሳዩ ዘንድ አልቻሉም፡፡
አንተ ግን ፍቺን ትሰጥ ዘንድ፥ የተቋጠረንም ትፈታ ዘንድ እንድትችል ሰምቻለሁ፤ አሁንም ጽሕፈቱን ታነብብ ዘንድ፥ ፍቺውንም ታስታውቀኝ ዘንድ ብትችል፥ ሐምራዊ ግምጃ ትለብሳለህ፥ የወርቅም ማርዳ በአንገትህ ዙሪያ ይሆንልሃል፥ አንተም በመንግሥት ላይ ሦስተኛ ገዥ ትሆናለህ።››
የዚያን ጊዜም ዳንኤል መለሰ በንጉሡም ፊት እንዲህ አለ፤
‹‹ስጦታህ ለአንተ ይሁን፥ በረከትህንም ለሌላ ስጥ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ ፍቺውንም አስታውቃለሁ፤
የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው።››
(ትንቢተ ዳንኤል ምዕ. ፭)፤
- አይሁዳውያን ታዳጊ ፋርሳዊው ቂሮስ
በዛችው ሌሊት የባቢሎንን መንግሥት ለመውጋት አድፍጦ ይጠባበቅ የነበረው የፋርስና የሜዶም መንግሥት የንጉሥ ቂሮስ ሰራዊት የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር በደረቅ መሬት ተሻግሮ የባቢሎንን ንጉሥ ብልጣሶርን ገደሉት፡፡ ፋርሳውያኑ የባቢሎንን ግዛትንም በቁጥጥራቸው ስር አዋሉት፡፡ ‹‹ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች፤›› እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ ያ በግርማውና በክብሩ የተፈራው የባቢሎን መንግሥት በትዕቢቱና በበደሉ የተነሳ በአንድ ሌሊት መንግሥቱ ተገረሠሠ፤ በፈንታውም የፋርስ መንግሥት ተተካ፡፡
መጽሐፍ እንደሚልም፤ የፋርስ መንግሥት ኢትዮጵያን እና ሕንድን ጨምሮ 127 አገራት ላይ የሰለጠነ ገናና መንግሥት እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ የፋርስ መንግሥት በመለኮታዊ ዕቅድ መሠረት ለአይሁዳውያን ትልቅ ተስፋን ነበር ይዞላቸው የመጣው፡፡ ‹‹አቤቱ የሆነብንን አስብ!››፤ በማለት በመሪር ለቅሶና ዋይታ የአባቶቻቸውን አምላክ ሲማጸኑ የነበሩት አይሁዳውያን የነጻነታቸው የተስፋ ጎሕ ቀደደ፡፡
የፋርስ ንጉሥ የሆነው ቂሮስ መለኮታዊውን ሐሳብ/ዕቅድ እንዲያስፈጽም በእግዚአብሔር የተመረጠ እንደሆነ የኢሳይያስ መጽሐፍ እንዲህ ይመስክራል፤
‹‹ቂሮስንም እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ፤ እግዚአብሔር ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል፦ በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም አደርጋለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፡፡››
(ትንቢተ ኢሳይያስ ፵፬)፤
በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ አማካኝነት አይሁዳውያኑ ከ፸ ዓመታት ምርኮና ግዞት ወጥተው ነጻነታቸውን ተጎናጸፉ፤ የፈረሰውንም ቤተ-መቅደሳቸውንም ይሠሩ ዘንድ ከፋርስና ሜዶም መንግሥት ፈቃድን አገኙ፡፡ አይሁዳውያኑ ከፈለጉ ወደ አባቶቻቸው ምድረ ርስት ከወደዱም በፋርስ መንግሥት ግዛት ይኖሩ ዘንድ ሙሉ ፈቃድ ተቸራቸው፡፡
የመጽሐፈ ዕዝራ ጸሐፊ፤ ንጉሥ ቂሮስ በባቢሎን ምድርና በዙሪያዋ የተበተኑ አይሁዳውያን ወደ አባቶቻቸው ምድር ይመለሱ ዘንድና የፈረሰው ቤተ-መቅደሳቸውን ይሠሩ ዘንድ ያወጣውን ዐዋጅ እንዲህ ከትቦታል፤
‹‹በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ።
የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤
በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን። የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ።
በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወርቅ በገንዘቦችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው።››
(መጽሐፈ ዕዝራ ምዕ. ፩)፤
ይሁን እንጂ ይሄ የፋርስ መንግሥት ንጉሥ ቂሮስ ለአይሁዳውያኑ የሰጠው የእረፍትና የመታደስ ዘመን፣ በእርሱ ፈንታ በተተካው በንጉሥ አርጤክስ ዘመን የንጉሡ ከፍተኛ ባለሥልጣን/ባለሟል በሆነው ሰው በኩል አንድ ትልቅ አደጋ ተጋረጠበት፡፡ ይኸውም ሃማ የተባለ የፋርስ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን አይሁዳውያኑ ሕጋቸው ከሕጋችን የተለየ፣ የመንግሥትህ ሥጋትና አደጋ በመሆናቸው አይዳውያኑ በያለበት ታድነው እንዲገድሉ ንጉሥን አሳምኖ ዐዋጅ አስወጣ፡፡ ዐዋጁን በንጉስ ቀለበት አተመበት፡፡
በዚህ የእልቂትና የፍጅት ዐዋጅ የተነሳ በአይሁዳውያን ዘንድ ታላቅ ሽብርና መናወጽ ሆነ፡፡ የንጉሥ በር ዘበኛ የነበረው መርዶክዮስ ይህን የእልቂት ዐዋጅ- ዐዋጅን በዐዋጅ ሊሽር ከአባቶቹ አምላክ ጋር መከረ። በእርሱና በሕዝቡ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማስቀረትም መርዶክዮስ በውበቷ ወደር የሌላትንና ወገኑ የሆነችው አስቴር ወደ ንጉሡ ገብታ ዐዋጁን በመገልበጥ ወገኖቿን ትታደግ ዘንድ እንዲህ በሚል ብርቱ የአደራ ቃል አስጠነቀቃት፤
መርዶክዮስም አክራትዮስን ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው። አንቺ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
አስቴርም እንዲህ ብሎ ለመርዶክዮስ እንዲመልስ አዘዘችው። ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ፤ ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን አትብሉም፥ አትጠጡም፤ እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፤ ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ብጠፋም እጠፋለሁ። መርዶክዮስም ሄዶ አስቴር እንዳዘዘችው ሁሉ አደረገ፡፡
(መጽሐፈ አስቴር ፬)፤
መርዶክዮስማ በእርሱና በሕዝቡ ላይ የታወጀው የሞት ዐዋጅ ይገለበጥ ዘንድ የወገኑ የአስቴር መንገዷና ሐሳቧ ሁሉ ይቃና ዘንድ የንጉሡ ልብም ይቀበላትና ይራራለት ዘንድ በመርዶክዮስ አስተባባሪነት አይሁዳውያኑ ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሁሉም ለ3 ቀን ጾም ጸሎት ያዙ፡፡ የአባቶቻቸው አምላክ ጸሎታቸውን ሰምተው የሃማ የሞት ዐዋጅም ተገለበጠ፤ የንጉሡ ባለሟል ሃማ ለመርዶክዮስ መስቀያ ባዘጋጀው እንጨት ላይ እራሱ ተሰቀለበት፡፡ የአይሁዳውያኑ የሞት ዐዋጅ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ወደ ሕይወት ተቀየረ፡፡
የፋርስና የሜዶም መንግሥት፣ ነገሥታቱ ቂሮስና አርጤክስ አይሁዳውያን ከምድር ላይ እንዳይጠፉ ይህን የታሪክ ተውኔት በመለኮታዊው ዕቅድ መሠረት ለመፈጸም በቅተዋል፡፡
- የመሲሑን ልደት አብሳሪ ጥንታዊቷ ፋርስ/ኢራን
ከኢራን (ፐርሺያ) የመጣው ንጉሥ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፤
በመሲሕው/በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በቤተልሔም የተገኙት ነገሥታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ሊቃውንት ዘንድ ‹‹ሦስቱ ጠቢባን›› ወይም ‹‹ሰብአ ሰገል›› ተብለው ይታወቃሉ፡፡
በማቴዎስ ወንጌል ገለጻ መሠረትም፤ ከምሥራቅ የመጡ ጠቢባን አንድ ኮከብ ተከትለው ወደ ቤተልሔም በመሄድ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ለተወለደው ለጌታችንና ኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ፤ ወርቅ፣ ዕጣን እና ከርቤ እንደ ስጦታ አቀረቡ፡፡ ከእነዚህ ሦስት ጠቢባን/ነገሥታት መካከል ደግሞ አንደኛው የአሁኗ ኢራን የዛን ጊዜዋ ፋርስ መንግሥት ንጉሥ የነበረው ጋስፓር ነው፡፡ በብዙ የክርስቲያን ታሪኮች ውስጥ እርሱ የፐርሺያ (ዛሬ ኢራን) ንጉሥ ወይም የፐርሺያ ጠቢብ መሆኑ ይገለጻል፡፡
በጥንታዊ ፐርሺያ ውስጥ “Magi” ተብለው የሚጠሩ ሰዎች የኮከቦችን እንቅስቃሴ የሚመረምሩ ጠቢባን ነበሩ፡፡ እነሱ የቤተልሔም ኮከብን በማየት አዲስ ንጉሥ መወለዱን እንደ ምልክት ተረዱ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቃውንት አስተምህሮ ከሆነ ደግሞ፤ ፋርሳውያኑ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ትንቢት በፋርስና በሜዶም ዘመን መንግሥት ‹‹የጠቢባን ሁሉ አለቃ›› ሆኖ በተሾመው በአይሁዳዊው ዳንኤል መጽሐፍ አማካኝነት መረዳታቸውን ይናገራሉ፡፡
ይህን የቀደሙ አባቶቹን ታሪክ ትውፊት በደንብ የመረመረው ፋርሳዊው ጋስፓር ከኢትዮጵያና ከሕንድ ጠቢባን ጋር በመሆን ወደ ቤተልሔም በመጓዝ ለመሲሑ የዕጣን ስጦታ እንዳቀረበ ይነገራል፡፡ የፋርሳዊው የዕጣን ገጸ-በረከት የክርስቶስን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ/መለኮታዊነትን እና የአዲስ አዲስ ካህን መሆኑን የሚያመለክት ምልክት መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን ያስተምራሉ፡፡
የማቴዎስ ወንጌል ውስጥ በቀጥታ እነዚህ ሰዎች ነገሥታት እንደነበሩ ወይም ሦስት እንደነበሩ አይጠቀስም፤ ነገር ግን ‹‹ከምሥራቅ የመጡ ጠቢባን›› ብቻ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ነገር ግን በኋላ በክርስቲያናዊ ባህል ውስጥ እነሱ የዓለም ታላላቅ ሥልጣናትን የሚወክሉ ሦስት ነገሥታት እንደሆኑ ተተርጎመ፡፡ እነዚህም ፐርሺያ (የአሁኗ ኢራን)፣ ኢትዮጵያ (አፍሪካ)፣ ህንድ ወይም እስያ የሚወክሉ እንደሆኑ ይታሰባል፡፡
- እንደ ማጠቃለያ
ከሰሞኑን በአሜሪካና በእስራኤል በጥምረት ጦርነት የተከፈተባት የጥንቷ ፋርስ የዛሬዋ እስራኤል በሰው ልጆች የሺሕ ዘመናት ታሪክ ውስጥ የመለኮትን ዕቅድ በመፈጸምና በማስፈጸም ትልቅ ድርሻ ያላት ጥንታዊት አገር መሆኗን ልብ ይሏል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ እስራኤልን ከምድረ-ገጽ/ከካርታ ላይ ካልጠፋው እረፍት የለኝም ያለችው የሺሕ ዘመናት ታላቅ ታሪክ እና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው ፐርሺያ/ፋርስ/ኢራን ከአይሁዳውያኑ ከዋንኛ አገሯ ከሆነችው አሜሪካ ጋር ጋር የገባበችበት ጦርነት ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ወይም የታላቁን የአርማጌዶንን ጦርነት የሚያዋልድ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዘንድ ይነገራል፡፡
የሆኖ ሆኖ ግን እስራኤልና አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ኢኮኖሚ ቀውስንና መናጋትን ያስከተለ ክስተት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በዚህ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታታዮች በጸሎት እና በጾም ፈጣሪያቸውን በሚማጸኑባት በዚህች የተቀደሰ ወራት ፈጣሪ፣ የሰላም አለቃ ለዓለማችን፤ ለምድራችን ሰላምን ይሰጥ ዘንድ በመመኘት ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
ሰላም! ሻሎም!
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 230 መጋቢት 2018 ዓ.ም
