የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (IRGC) በደቡባዊ ኢራን በምትገኘው ባንደር አባስ የወደብ ከተማ አቅራቢያ አሜሪካ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት “የአሜሪካ የጦር ሰፈርን” ኢላማ ማድረጉን አስታወቀ።
ይህ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የተቀሰቀሰው ግጭት በቀጣናው ሰፊ አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተው አብዮታዊ ዘቡ የአሜሪካን ጥቃት “ከንጋት በፊት የተፈጸመ ትንኮሳ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ጥቃቱም በባንደር አባስ አየር ማረፊያ እና የወደብ ተቋማት ዳርቻ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ገልጿል።
በኢራን ተስኒም የዜና ወኪል በኩል የወጣው የአብዮታዊ ዘቡ መግለጫ እንደጠቆመው፤ የአጸፋ ጥቃቱ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 10፡50 ላይ የተፈጸመ ሲሆን፣ ማንኛውም ተጨማሪ የአሜሪካ “ትንኮሳ” ካለ “የበለጠ ወሳኝ” ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠንቅቋል።
ይሁን እንጂ መግለጫው የተመታው የአሜሪካ የጦር ሰፈር የት እንደሚገኝ በዝርዝር አልጠቀሰም። ሮይተርስ አብዮታዊ ዘቡን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ለውጥረቱ መባባስ ኃላፊነቱን የሚወስደው “ጥቃት አድራሹ” ወገን ነው።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ባለሥልጣናት ያከናወኑት ወታደራዊ እርምጃ “የመከላከያ እና የተገደበ” እንደነበር ገልጸዋል። አሜሪካ በባንደር አባስ አቅራቢያ የሚገኝ የድሮን መቆጣጠሪያ ጣቢያ መምታቷን የገለጹት ባለሥልጣናቱ፤ ይህም የተደረገው አራት የኢራን የጥቃት ድሮኖችን ካከሸፉ እና አምስተኛው ድሮን በሆርሙዝ ስትሬት አቅራቢያ በሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ ኃይሎች እና የባሕር ትራፊክ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ለመከላከል እንደሆነ ዳውን (Dawn) ዘግቧል።
ከዚህ ጥቃት በተያያዘ በሆርሙዝ ስትሬት የባሕር ላይ ውጥረት መንገሡን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ተስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ የኢራን የባሕር ኃይል ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ቅድመ ቅንጅት ሳያደርጉ ወደ ባሕረ ሰላጤው ለመግባት የሞከሩ አራት መርከቦችን ገጥሟቸዋል።
አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ወታደራዊ ባለሥልጣንን የጠቀሰው ዘገባው፤ መርከቦቹ መጀመሪያ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለታቸው የኢራን ኃይሎች የማስጠንቀቂያ ተኩስ እንዲተኩሱ እና መርከቦቹ እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ገልጿል።
በተያያዘም ኩዌት በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ይዞታዎችን ኢላማ ካደረጉ የኢራን የአጸፋ ጥቃቶች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የታመኑ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን የአየር መከላከያ ሥርዓቷ ማክሸፉን አስታውቃለች።
አልጀዚራ እንደዘገበው፤ በዓለም እጅግ ወሳኝ በሆነው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በሆርሙዝ ስትሬት ላይ የሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሊስተጓጎል ይችላል በሚል ስጋት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
