የቀድሞው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጅ፣ የኤርትራን 35ኛ ዓመት የነጻነት በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት፣ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር ላይ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።
ታላቁ የኤርትራ ህዝብ ለነጻነቱ የከፈለውን መስዋዕትነትና ጽናት ያደነቁት አንጋፋው ዲፕሎማት፣ በሌላ በኩል ግን ዜጎቹን መብት በመንፈግ ሀገሪቱን ወደ ግዙፍ እስር ቤትነት ቀይሯል ያሉትን የአስመራውን አገዛዝ ክፉኛ አውግዘዋል።
ይህ የናጅ ጠንካራ አስተያየት ዋሽንግተንና አስመራ የቆየውን የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማደስና ማዕቀቦችን ለማንሳት ፍንጭ እያሳዩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት መውጣቱ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል።
ዲፕሎማቱ በመልእክታቸው ያልተጠበቀና ስትራቴጂካዊ አንድምታ ያለው የፖለቲካ ትንበያ ያጋሩ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከአሜሪካ ጋር የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር በራቸውን ክፍት ያደርጋሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሆኖም ናጅ እንደሚያመለክቱት፣ ይህ ዲፕሎማሲያዊ መቀራረብና ግልጽነት ለኤርትራ መንግስት መረጋጋትን ሳይሆን የአገዛዙን ውድቀት የሚያፋጥን ቀዳዳ ይፈጥራል።
አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን ብታሻሽል እንኳን፣ የሚመጣው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለኢሳያስ መንግስት መውደቂያ መንገድ ጠራጊ እንደሚሆን በመጠቆም የተለየ የዲፕሎማሲ እይታን አንጸባርቀዋል።
