በአሜሪካ ፍሎሪዳ (ታልሃሲ) በተካሄደው 46ኛው የዓለም አገርአቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ የተጠሪ ተቋማት፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የዘርፍ ኃላፊዎች በተገኙበት አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
የአትሌቲክስ ቡድኑ ሦስት የወርቅ፣ ሁለት የብርና ሁለት የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያ በማስመዝገብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ ሻምፒዮናውን በበላይነት ያጠናቀቀችው ደግሞ ኬንያ ሆናለች፡፡
በሻምፒዮናው ላይ ከ52 አገሮች የተውጣጡ 485 አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ በቪዛ ክልከላ ምክንያት ከ28 አትሌቶች በ14 አትሌቶች ብቻ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ፣ በወጣት ወንዶች በአንድ አትሌት፣ በወጣት ሴቶች በሦስት አትሌቶች በሁለቱ የውድድር ዓይነቶች በቡድን መገኘት የነበረበት ሜዳሊያ አለማግኘቷም ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው 8 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶችና ሴቶች በቡድን ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ፣ በግል በሴቶች ማርታ ዓለማየሁ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በአዋቂ ወንዶች በበሪሁ አረጋዊ አማካይነት የብር እንዲሁም በወጣት ሴቶች በወሰኔ አሰፋ አማካይነት የብር ሜዳሊያና በድብልቅ ሪሌ ማለትም (4 በ2 ኪሎ ሜትር) በቡድን የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም በ1ዐ ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች በሠናይት ጌታቸው አማካይነት የነሐስ ሜዳሊያ መመዝገቡ ታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የልዑካን ቡድኑ መሪ ወ/ሮ ሳራ ሐሰን በአጠቃላይ ከዝግጅት፣ ከጉዞ፣ ከውድድርና ከሥልጠና ጋር በተገናኘ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ አገር አቀፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ከአትሌቶቻችን የግል ጥንካሬና ጽናት በስተቀርበዝግጅትም ሆነ በሥልጠና እንዲሁም ወጥና ቋሚ ብሔራዊ ቡድን ከመገንባት አኳያ ችግር ውስጥ ነን፡፡ ቁጭ ብለን በችግሮቻን ዙሪያ ተወያይተን መፍትሔ ማበጀት ይኖርብናል፣ ለአትሌቲክሳችን መፍትሔው ትኩረት ለአትሌቶቻችን መስጠት ነው፡፡
በተጓዝንባቸው አገሮች መወዳደሪያ ሥፍራዎችን ተመልክተናል፣ ልዩነታችን ሰፊ ናቸው፣ ዓለም በብዙ መልኩ ርቆን ሔዷል፡፡ እኛ በድንቅ አትሌቶቻችን የግል ጥረት እንጂ፣ ከመወዳደሪያ ሥፍራዎች ጋር በተገናኘ ዓለም በብዙ መልኩ ርቆን ሄዷል፤›› በማለት አትሌቲክሱ እንደ አገር ያለበትን ተግዳሮት ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጉባዔ አስረድተዋል፡፡
ልዑካን ቡድኑን የተቀበሉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፣ ‹‹ድሉ እጅግ የኮራንበት ነው፣ ሰንደቅ ዓላማችንን በዓለም አደባባይ ከፍ አድረጋችሁ ስላውለበለባችሁ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም አመሰግናለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም በአዲሱ ሪፎርም የመጣ ውጤት በመሆኑ ቀጣይነት ያለው የታዳጊና ተተኪ ስፖርተኞች ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚጠበቅቸው ጭምር አሳስበዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ጌቱ ገረመው (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ አትሌቶቹ በተለያዩ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ዝግጅትና ልምምድ በማድረጋቸውና በቅንጅት በመሥራታቸው በአጠቃላይ አትሌቶቹ ጥሩ መንፈስና ስሜት ኖሯቸው እንዲጓዙ በመደረጉ፣ ለዚህ ድል ትልቁን ድርሻ መወጣቱን ተናግረዋል፡፡ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሠራልም ብለዋል፡፡
ከረዥም ዓመታት በኋላ ወደ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት የመጡት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በበኩላቸው፣ እሳቸው ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር ከሥልጠናው በፊት፣ የጋራ ዕቅድ ከማውጣት ባለፈ የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት አትሌቶቹ ብሔራዊ ስሜት ኖሯቸው በአንድነት እንዲሠሩ በማድረጋቸው ውጤቱ ሊመዘገብ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ከሪፖርተር በደረጀ ጠገናው
