ቦታው መኖርያ ቤቱ ነው። ፊት ለፊቴ ተቀምጧል። አጠገቡ ባለቤቱ ክብርት አርቲስት አምለሰት ተቀምጣለች። ራት ቀርቧል። ጥያቄ ጠየኩት…
” ቴዲ ላንተ የተለየ ቅዱስ ስፍራ የት ነው? “
አስቦ መለሰልኝ… ” ኢትዬጵያ ! ” ብሎ ዝም አለ።
ያልገባው መሰለኝ። ደግሜ ጠየኩት…
” ማለቴ ከቅዱስ ስፍራዎች ላንተ የተለየው ቦታ የት ነው? “
አሁንም እንደተረጋጋ መለሰልኝ
” ኢትዬጵያ ! ” አለና አንገቱን ደፋ አደረገ።
ለመጨረሻ ጊዜ ሞከርኩኝ… እያስረዳሁት
” ከአክሱም፣ ከላሊበላ፣ ከግሸን ከመሳሰሉት አንተ ልዩ ቅዱስ ቦታ የምትለው የትኛውን ነው? “
ቴዲ ፈገግ ብሎ አየኝና ” ሁሉንም ቅዱስ ስፍራዎች አከብራለሁ! ለእኔ ቅዱስ ቦታ ኢትዮጵያ ናት ! ” አለኝ።
የክብር ዶክተር ቴዎድሮስ ካሳሁን እኔ ቀርቤ እንዳየሁት እጅግ በጣም መልካም ሰው ነው።
1. ቴዲ ለየትኛውም ብሔር ጥላቻ ወይም ንቀት የለበትም። የተለየ የብሔር ፍቅርም የለውም። ለእርሱ ሁሉም ኢትዬጵያውያን እኩል የተወደዱ፣ የተከበሩ ናቸው።
2. ቴዲ አፍሮ የሚተማመነው በችሎታው፣ በዝናው ወይም በገንዘቡ አይደለም። በሰራዊት ጌታ በልዑል እግዚአብሔር ግን እጅጉን ይተማመናል። ” የሚጠብቀኝ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ነው” ብሎኛል።
3. ቴዲ ክርስቶስን ይወዳል። በሳሎኑ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው የአለም መድሃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በትልቁ ተስሏል። ቴዲ ያንን ስዕል እያየ ይተርከዋል፣ ይገልጠዋል… የጌታ እናትም የልብ ወዳጁ ናት!
4. ቴዲ አፍሮ መዝሙር ያዳምጣል። የሚወዳቸውን ሁለት የድሮ መዝሙሮች ከፍቶ አሰምቶኛል። በራሱ ሐይማኖት ባይደራደርም ለሁሉም ሐይማኖቶች ክብር አለው። በራሱ ሐይማኖት ያሉትን የገዳም አባቶች ያከብራቸዋል፣ ይሰማቸዋል።
5. ቴዲ ሲናገር ቁጥብ ነው። ቃላት አያባክንም። በሚገባ አስቦ ነው የሚናገረው። ቃላቶቹን ያሻቸዋል፣ ያሽሞነሙናቸዋል! አጣፍጦ፣ አሳምሮ፣ ቀምሮ ያወጣቸዋል። ቴዲ ሲያወራ መስማት እንደ ሙዚቃው ነው።
6. ቴዲ አፍሮ ለትዳሩ ታማኝ ነው። አምለሰትን በስስት አይን ያያታል። እርሷም ሳራ አብርሃምን ‘ ጌታዬ ‘ ብላ እንዳከበረችው ባልዋን በፍቅርና በክብር ትንከባከበዋበች። ባልና ሚስቱን በቤታቸው ማየት፣ በፍቅር ሲያወሩ መስማት እጅግ ደስ ያሰኛል።
7. ቴዲ ያለውን ዝና የሚያውቀው አይመስልም። ወይም ትኩረት አይሰጠውም። ስለሱ ለማውራት ስሞክር ወሬውን ፈጥኖ ይቀይረዋል። መሞገስን ይሸሻል! በጣም ትሁት ነው! ዝምተኛነቱ ኩሩ ሊያስመስለው ይችላል። ግን ቴዲ ኩሩ አይደለም! ሰውን በሁለት እጁ የሚጨብጥ፣ ጎንበስ ብሎ እጅ የሚነሳ ጨዋ ሰው ነው።
8. ለቴዲ ሙዚቃ ህይወቱ ነው! በጣም ከፍተኛ የሙዚቃ ክህሎት Musical Intelligence እንዳለው ይታወቃል። ኑሮው ከቤቱ ወደ ስቱዲዬ፣ ከስቱዲዬ ወደ ቤቱ ነው። የሙዚቃ ስራዎቹ የሚወደዱት በስጦታው ላይ ትጋት ተጨምሮባቸው ነው። ቴዲ የሙዚቃ Genius ይመስለኛል !
9. ቴዲ አፍሮ መጻህፍትን ያነባል። ለማንበብ ጊዜ አለው። ታሪክ ይወዳል። ታሪክን በጥልቀት ይመረምራል፣ ይፈትሻል፣ ያሰላስላል። ቴዲ ጥሩ አሰላሳይ (Thinker) ነው።
10. ከቴዲ ጋ ባሳለፍኳቸው ሰዓታት የትኛውንም የፖለቲካ ሰው አንስቶ አላወደሰም፣ አልተቃወመም። ፖለቲካዊ አስተያየቶችን ሲሰጥ አልሰማሁትም።
11. ቴዲ አፍሮ ቀርበው ሲያዩት በሚዲያ ከሚታየው በላይ ልዩ ሞገስ፣ ውበትና ክብርን የተላበሰ ሰው ነው። ጃኬት በቲሸርትና በጂንስ ለብሶ ዘውድ የጫነ፣ ካባ የደረበ ፣ በትረ መንግስት የጨበጠ ንጉስ ይመስላል።
12. ቴዲ ሐሙስ ከሚወጡት ስራዎቹ ሀገራዊ የሆኑትን ሁለቱን ከፍቶ አሰምቶኛል። እጅግ በጣም አስደናቂ ናቸው። ለሀገርና ለህዝብ ያለውን ፍቅር የሚያንፀባርቁ ታሪካዊ ስራዎች ናቸው።
የክብር ዶክተር ቴዎድሮስ ካሳሁን ስራውን እንዲሰራ እንፍቀድለት። ቴዲን መጥላት ይቻል ይሆናል። በቴዲ መጠላት ግን አይቻልም። ንፁህ በሆነው ልቡ ውስጥ ጥላቻ የለም። ” ፍቅር ያሸንፋል ” ሲል በፍቅር ተሞልቶ ነው። ማንንም የመጉዳት አቅም የለውም። ወንድማችንን ያለ ልዩነት እንቀበለው። ሊወደድ፣ ሊደነቅ፣ ሊከበር የሚገባው ስጦታችን ነው!
ዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ
ዝምተኛው ቴዲ አፍሮ !
Date:
