በሰሜን ጋዛ የመጨረሻው ሆስፒታል በእስራኤል ትዕዛዝ ስራዉ ለማቆም መገደዱ ተገለፀ።
በሰሜን ጋዛ ግዛት የመጨረሻው የጤና አገልግሎት የሚሰጠው ሆስፒታል የእስራኤል ጦር በአስቸኳይ እንዲለቅ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተከትሎ ከአገልግሎት ውጪ መሆኑን የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ህሙማን ጃባሊያ ከሚገኘው አል-አውዳ ሆስፒታል ወደ ሌላ ስፍራ ተወስደዋል።
እስራኤል እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጠችዉ ምላሽ ባይኖርም በሆስፒታሉ ያሉ ሰዎች የእስራኤል ጦር ሃይል ሊሰነዝረዉ በሚችለዉ ጥቃት ፈርተዉ መሸሻቸዉን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው ባለፉት ሁለት ሳምንታት የቀጠለው ግጭት ሆስፒታሉን ጎድቷል፣ ተደራሽነቱን አቋርጧል ብሎም ህሙማን ህክምና እንዳያገኙ አድርጓል።
ከ27 የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ጤና ጣቢያ ዘጠኙ በስራ ላይ እንደነበሩ ተመላክቷል።
ኤጀንሲዉ ጋዛን “በምድር ላይ እጅግ የተራበች ቦታ” ሲልም ጠርቷል።
እስራኤል በተያዘዉ የፈረንጆቹ አመት የሁለት ወራት የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረገች በኋላ ጥቃቷን በጋዛ አጠናክራ ቀጥላለች።
