ባሳለፍነው ግንቦት 3 ቀን 2017ዓ.ም “የመድረክ ማስታወሻ ከአዲስ አበባ እስከ ሰሜን አሜሪካ” የሚል ርዕስ የሰጠውን መፅሐፍ ለአንባቢያን ያበቃው ጋዜጠኛውና የመድረክ መሪ ወንድወሰን ከበደ በኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 አማካይነት ተዘጋጅቶ ለአድማጭ በሚቀርበው “ዘጠናዎቹ በ97.1” መሰናዶ ጋር ቆይታ አድርጓል።
መፅሐፉ የ25 ዓመታት መድረክ በመምራት ሁነቶችን በማዘጋጀት እንዲሁም በስፖርት ጋዜጠኛነት ያለፈባቸውን ጉዞዎች እንደሚያወሳ የገለፀው ወንድወሰን በዘጠናዎቹ ወቅት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የነበረው ቆይታ ሰፊውን ገፅ እንደሚይዝ አስታውቋል።
በ1990 ዎቹ ዘመን ዛሬ ላይ ሥመ-ጥር የሆኑ ድምፃውያውን እና ኮሜዲያን በኤግዝቢሽን ማዕከል ስራዎቻቸውን በማቅረብ ከጥበብ አፍቃሪያን ጋር የተዋወቁበት እንደነበር አንስቷል።
“እኛ እና እኛ ኢትዮጵያ የተሰኘውና ለተከታታይ አራት ዓመታት የዘለቀው የሙዚቃ ድግስ ግን ከፍተኛውን ስፍራ እንደሚይዝ ጠቁሟል።
ከመድረኩ ሙዚቃ እና የኮሜዲ ዝግጅት ከመኖሩ ባለፈ የተለያዩ ሽልማቶች ተሰናድተው ይቀርቡ እንደነበር ያስታወሰው የመፅሀፉ ደራሲ በ1990 ዓ.ም ጌራወርቅ ነቃጥበብ ” አመጣኝ መውደድሽ በሚለው አልበም፣ በ1991ዓ.ም ላፎንቴኖች ” እንዲህች እንዲህች” አልበም ስራ፣ በ1992 አለማየሁ ሄርጶ እና ጎሳዬ እንዲሁም ሀይልዬ ታደሰ ኮከብ ሆነው የቀረቡበት መድረክ እንደነበር አንስቷል።
ማስታወሻዎችን በጥንቃቄ የመያዝ እና በአግባቡ የመሰነድ ልምድ እንዳለው የሚያወሳው ይህ መፅሐፍ እውን እንደሚሆን ያኔ ላይ ብረዳ ከእነዚህም ከፍ ያሉ ማስታወሻዎች ይካተቱበት እንደነበር አስታውቋል።
በእዚህም ሳቢያ ሳይዛቸው የቀሩ ማስታወሻዎች መኖራቸው እንደሚያስቆጨእ በቆይታው ያነሳው ወንድወሰን ከበደ ያም ሆኖ ግን ተከታታይ “የመድረክ ማስታወሻ” ቅፆች እንደሚኖሩ ገልጾልናል።
“የዘመናት ልፋቴን አይቶ እግዚአብሔር አክብሮኛል የሚለው” ጋዜጠኛና የመድረክ መሪው ወንድወሰን ከበደ የመፅሐፉ የመረቃ መድረክ ላይ የታደሙ እንግዶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን አመሰግኗል።
ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1
