የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ከዓመታዊ የትርፍ 90 በመቶውን እንዲያከፋፍሉ ሊደረግ ነው

Date:

የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ተብለው የሚቋቋሙ ፈንዶች ከዓመት ትርፋቸው ቢያንስ ዘጠና በመቶውን ለሰነደ ሙዓለ ንዋይ ባለቤቶች በትርፍ ድርሻ መልክእንዲያከፋፍሉ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ረቂቅ መመርያ አዘጋጀ፡፡

ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ረቂቅ መመርያ፣ በካፒታል ገበያ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋፋትና ባለሀብቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

ባለሥልጣኑ ቁጠባን ወደ ኢንቨስትመንት ለማምራትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማስፋት በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 ያዘጋጀው ” የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ ረቂቅ መመርያ” እንደሚያሳየው፣ የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ ማለት፣ ከበርካታ ባለሀብቶች የተሰበሰበ ገንዘብ በአንድ ላይ በመመደብ በባለሙያዎች የሚተዳደርና የአክሲዮኖች፣ የቦንዶች ወይም ሌሎች የፋይናንስ ሰነዶች ውህድ በመፍጠር ከትርፍ ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢንቨስትመንት ሥልት ነው።

በዚህም ለሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ፈንድ ለመመዝገብ ከሚያበቁ መሥፈርቶች አንዱ፣ ከፈንዱ የተጣራ የሀብት ዋጋ ቢያንስ 80 በመቶ ገቢ የሚያስገኝ ሪል ስቴት ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚል መሆኑ በረቂቁ ተደንግጓል።

ለእያንዳንዱ የሒሳብ ዓመት ሊከፋፈል ከሚችለው ትርፍ ወይም ገቢ ቢያንስ 90 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ፣ ለሰነደ ሙዓለ ንዋይ ባለቤቶቹ በትርፍ ድርሻ መልክ ማከፋፈል እንደሚኖርበት ያስገድዳል።

ገቢ የሚያስገኝ ሪል ስቴት ላይ ኢንቨስት ያልተደረገው ቀሪ ሒሳብ በሪል ስቴት ልማት ንብረት፣ በሰነደ መዓለ ንዋዮች፣ አግባብነት ባላቸው የገንዘብ ሰነዶች ወይም በጥሬ ገንዘብ ላይ ኢንቨስት ሊደረግ እንደሚችል በረቂቅ መመርያው ሠፍሯል።

የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ከፈንዱ ጠቅላላ ሀብት ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ በአንድ የገቢ ምንጭ፣ ወይም ገቢ ከሚያስገኝ ሪል ስቴት የገንዘብ ፍሰት ምንጭ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደማይቻል በረቂቅ መመርያው ተደንግጓል።

ሆኖም የሚኖረው የኢንቨስትመንት ክምችት፣ የንብረቱን የሥጋት መግለጫ ከግምት በማስገባትና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ባለቤቶችን የማይጎዳ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ፈንዱ ከጠቅላላ ሀብቱ ውስጥ ከሃያ በመቶ (20 በመቶ) በላይ የሚሆነውን በአንድ የገቢ ምንጭ ወይም ገቢ ከሚያስገኝ ሪል ስቴት የገንዘብ ፍሰት ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግ ሊፈቅድ ይችላል።

ረቂቅ መመርያው እንደሚያስረዳው፣ አንድ ፈንድ መበደር የሚችለው፣ የብድር መጠን ጠቅላላ የፋይናንስ ሰነዶችን፣ ጥሬ ገንዘብንና ሌሎች በባለሥልጣኑ የተፈቀዱ ማናቸውንም የሀብት ዓይነቶችን ያካተተ የፈንዱ ጠቅላላ የሀብት ስብጥር (ፖርትፎሊዮ) ከሃያ በመቶ ካልበለጠ ነው ይላል።

የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ፈንድ ካለው ጠቅላላ የፈንድ ፖርትፎሊዮ እስከ አርባ በመቶ ያህል ሊበደር እንደሚችልም ረቂቁ ደንግጓል።

የጋርዮሽ ገንዘብ ፈንድ፣ የገንዘብ ገበያ ፈንድ፣ በሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገበያ የሚሸጥ ፈንድ፤ አማራጭ የኢንቨስትመንት ፈንድና ባለ ልዩ ስያሜ ፈንድ፣ ከሪል ስቴት ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ሌሎች የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ ዓይነቶች መሆናቸውን ረቂቁ ያስረዳል።

ማንኛውም ፈንድ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ምዝገባ የምስክር ወረቀት ካገኘበት ጊዜ አንስቶ በስድስት ወራት ውስጥ ከጠቅላላ ሀብቱ ቢያንስ 30 በመቶውን ኢንቨስት ማድረግ እንዳለበትም በረቂቅ መመርያው ተካቷል።

ሆኖም እንደ ገበያው ሁኔታ መዋዠቅ ወይም ከፈንዱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ሁኔታዎችን ጨምሮ ልዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙና ለተጨማሪ ጊዜ ማራዘሚያው በቂ ምክንያት ሲኖር፣ ባለሥልጣኑ የስድስት ወሩን የጊዜ ገደብን ከስድስት ወር ለማይበልጥ ተጨማሪ ጊዜ ሊያራዝመው እንደሚችል ረቂቅ መመርያው ይገልጻል።

የጋራ ፈንድ ረቂቅ መመርያ፣ ኢንቨስተሮች ቁጥጥር በሚደረግበት በባለሙያ በሚመራና በቀላሉ ተደራሽ በሆነ መልኩ በካፒታል ገበያ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያስችል ዋና መሣሪያ መሆኑ በረቂቁ ተደንግጓል።

ለኢንቨስተሮች ጥበቃ በማድረግ የገበያውን ፍትሐዊነት፣ ታማኝነትና ቅልጥፍና እያረጋገጠ ካፒታልን ለማንቀሳቀስ፣ የፋይናንስ ፈጠራን ለማስፋፋት፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት የአደጋ ሥጋቶችን ለመጋራት የሚያስችል የቁጥጥር ማዕቀፍ በመሆን እንደሚያገለግልም ተገልጿል።

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፡ ረቂቁን በተመለከተ ያላቸውን አስተያየት እስከ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ፣ በሕዝባዊ ምክረ ሐሳብ መስጫ መድረክ ላይ በቀጥታ እንዲያጋሩ ጥሪ አቅርቧል።

ethiopianreporter

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...