የቅራኔ ደረጃዎች

Date:

ግዮን መጽሔት :- የቅራኔ ደረጃዎች (Conflicts Stages) የተሰኘው የቅራኔዎች መተንተኛ መሣሪያ የተገነባው አብዛኛዎች ቅራኔዎችና ግጭቶች በድንገት የተፈጠሩ ሳይሆን “ታሪክ” ያላቸው ናቸው በሚል እሳቤ ላይ ነው።

ለምሳሌ ዛሬ ግጭት ውስጥ የገቡ ማኅበረሰቦች ቢኖሩ የግጭቱ ስረ ምክንያቶች ለዓመታት የተካበቱ ቁርሾዎች ድምር ውጤት ሊሆን ይችላል። በግለሰቦች መካከል ያለ ጠብም እንደዚሁ ነው።

ዛሬ በሆነ ሰበብ ግጭት ቢነሳ ከዛሬው ሰበብ ባሻገር ለዓመታት ታፍነው የቆዩ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ ይቻላሉ። ስለሆነም ለቅራኔዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት ለዛሬ ጠብ ብቻ ሳይሆን ለትላንቱም ቁርሾ መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል።

እንደ ቅራኔ ተንታኝ ባለሙያዎች እምነት ቅራኔዎች በአምስት የተለያዩ ደረጃዎች ያልፋሉ: (1) ቅድመ-ግጭት (pre-conflict)፣ (2) ግጭት (confrontation)፣ (3) ቀውስ (crisis)፣ (4) ውጤት (outcome)፣ እና (5) ድህረ-ግጭት (post-conflict)። እነዚህ አምስት ደረጃዎች በስዕል 1 ተመልክተዋል።

ስዕል1: የቅራኔዎች ደረጃ

ቅድመ – ግጭት ቅራኔዎች ፈጽሞ የሌሉበት ወቅት ነው ማለት አይደለም። ቅራኔዎች ፈጽሞ የሌሉበት ወቅት የለም። ቅድመ – ግጭት ቅራኔዎች ቢኖሩም ግኑኝነቶችን ለማበላሸት በሚችል መጠን ጎልተው ያልወጡበት ወቅት ነው።

በተለምዶ “የሰላም ወቅት” የምንለው ይህንን ጊዜ ነው። ቀጥሎ የሚመጣው የግጭት ወቅት በሆነ ሰበብ ታፍኖ የቆየው ቅራኔ ገሀድ የሚወጣበትና ግኑኝነቶች የሚሻክሩበት ጊዜ ነው። የቀውስ ወቅት ደግሞ ግኑኝነቶች በአጠቃላይ የሚቋረጡበት፤ የእርስ በርስ መጎዳዳት የበዛበት ወቅት ነው። የእርስ በርስ መጎዳዳት ውጤት እንደየቅራኔው ዓይነት ይለያያል።

በማኅበረሰቦች መካከል የተፍጠረ ቅራኔ ከሆነ የዜጎች ሞትና የአካል መጉደል፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ከውጤቶቹ መካከል ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ ታልፎ ግን የመስከኛ ድኅረ – ግጭት ወቅት ይመጣል፤ ይህም ራሱ ብዙ ደረጃዎች ያሉት ቢሆንም ሦስተኛ አካላት በአስታራቂነት ገብተውበት ሆነ ሳይገቡበት ግጭቱ የሚረግበት ጊዜ ነው።

በጣም በረዘመ ጊዜ ካየነው ከላይ በስዕል 1 የቀረበው ግጭት ሌላ ምክንያት ጨምሮ ተመልሶ የሚያንሠራራበት እድል አለ። እንዲያውም የአገሮች ታሪክ በአብዛኛው የግጭቶች ታሪክ ነው። ስዕል 2 ከ1950ቹ እስከዛሬ ያለውን የኢትዮያን የግጭቶች ዑደትን ያመላክታል፡፡

ስዕል 2: የቅራኔ ደራጃዎች በኢትዮጵያ – ለምሳሌነት ብቻ የቀረበ

ዛሬ አገራችን ውስጥ ያሉትን ቅራኔዎች ምንነት ለመረዳት የሚፈልግ ሰው ቢያንስ እስከ 1960 ዎቹ ወደኋላ ተመልሶ መመልከት ይኖርበታል።

የ1960ዎቹ ወጣቶች (1ኛ) መሬት በጥቂት ባለሀብቶችና በተቋማት ንብረትነት በመያዙ ገበሬው የሚያርሰው አጥቷልና መሬት ለአራሹ ይሰጥ፣ (2ኛ) ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ሆናለችና ብሔሮች ከእስር ተፈተው የራሳቸውን እድል ራሳቸው ይወስኑ፣ እና (3ኛ) የዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ ሲሉ የተደራጀ ተቃውሞ በንጉሱ አስተዳደር ላይ አቀረቡ።

ሦስቱም ጥያቄዎች በማርክሳዊ-ሌሊናዊ አስተምህሮ የተቃኙ ነበሩ። ይህንን ቅራኔ ንጉሠነገሥቱ በጊዜው መፍታት ባለመቻላቸው ወደ ቀውስ አመራ፤ በውጤቱም በቅራኔው ቀጥተኛ ተሳታፊ ያልነበረው ወታደራዊ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መጣ።

አዲሱ ወታደራዊ አስተዳደር ከላይ የተነሱትን ጥያቄዎች በመሰለው መንገድ በመፍታት ራሱንም ከማርክሳዊ ሌሊናዊ ርዕዮተ ዓለም ጋር በማስተዋወቅ ቅራኔውን አረጋጋው። ይሁን እንጂ ወታደራዊው አስተዳደር ጥያቄዎቻችንን አልመለሰም የሚሉ ወገኖች ቅራኔውን በተለየ መንገድ አስቀጠሉት።

ወቅቱ የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ነበርና ተፋላሚዎችም የየራሳቸውን ጎራ ያዙ። ቅራኔው “ቀይ ሽብር” እና “ነጭ ሽብር” ወደ ተባሉ የሽብር ዓይነቶች ተካረረ።

ከዚያም አልፎ የሽምቅ ውጊያዎች ተበራከቱ ከፍተኛ የእርስ በርስ እልቂት እና የንብረት ውድመት ደረሰ። በውጤቱም በ1983 ወታደራዊው አስተዳደር ከስልጣን ተወገደ፤ ኤርትራ ራሷን የቻለች አገር ሆነች፤ ኢትዮጵያ ቋንቋን መሠረት ያደረጉ የክልል መንግሥታት ስብስብ ሆነች።

ይህ ለጥቂት ዓመታት ቅራኔዎቹን አረጋጋ።  ከዓመታት በኋላ ግን ቀድሞውኑ የነበሩ ጥያቄዎች በተለየ መንገድ መቅረብ ጀመሩ። የመሬት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሀብት ክፍፍሉ ኢፍትሀዊ ነው፤ አዲሱ የክልሎች አደረጃጀት እኩልነትን በማስፋት ፋንታ ገዢዎችንና ተገዡዎችን ፈጥሯል፤ ዲሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ ናችው የሚሉ ስሞታዎች በዙ።

እነዚህን ቅሬታዎች በተደራጀ መንገድ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ተፈጠሩ። ምርጫ 97 እነዚህን ችግሮች መፍታት ሳይችል ቀረ። ቅራኔው በድጋሚ ተካሮ ሌላ የቀውስ ጊዜ ፈጠረ፤ በውጤቱም የሥርዓቱ ምሰሶ የነበረው ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት ፈረሰ፣ ህወሓት በተቃዋሚነት ተሰለፈ፤ ብልጽግና የሚባል ፓርቲ ተፈጠረ። ለጊዘው እዚሁ ቀውስ ደረጃ ላይ ነው ያለነው።

ይህ በአንድ አንቀጽ አጥሮ የቀረበው ብዙ መጻሕፍት የተፃፉበት እና ወደፊትም የሚፃፉበት ታሪክ ነው። እጅግ ያጠረ ቢሆንም እንኳን ለቅራኔ ተንታኝ አንድ መሠረታዊ ነጥብ ያስጨብጣል።

የዛሬ ችግሮቻችን ዛሬ የተፈጠሩ ሳይሆን ከድሮ ጀምሮ ሲንከባለሉ ቆይተው እኛ ዘንድ የደረሱ መሆናቸው ነው። ስለሆነም መፍትሔ ስንፈልግም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ እንድንፈልግ ይረዳናል።

ዛሬ አገራችን ለገባችበት ችግር ዘላዊ መፍትሔ ለመፈለግ ከድሮ ጀምሮ ሲያወዛግቡን ለቆዩ ሦስት ጉዳዮች መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል፡ (1) የመሬት (ባጠቃላይ የሀብት ክፍፍል) ጉዳይ፣ (2) የእኩልነት ጉዳይ (ምን ዓይነት አስተዳደር ነው የተሻለ እኩልነት የሚያሰፍንልን) ፣ እና (3) የሰብዓዊናዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጉዳይ።

ኢትዮጵያን የተጠቀምነውም በምሳሌነት ብቻ ነው፤ የትንተናው መሣሪያ ለማንኛውም ዓይነት ቅራኔ ማዋል ይቻላል። በተለይ ወጣቶች አንድ ቅራኔ ውስጥ እጃችሁን ከማስገባታችሁ በፊት የቅራኔውን ታሪክ ለማጥናት ብትሞክሩ ገንቢ ሚና ለመጫወት ያስችላችኋል።

***

ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በ ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን የሰላምና የግጭት ጥናቶች ባለሙያ ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ላይ ያላችሁን አስተያየት ycdfoundationethiopia@gmail.com  ወይም tkersmo@yahoo.com መላክ ትችላላችሁ።

የዚህ ፁሑፍ እስፖንሰር :- ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን ሀገር በቀል የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን ከተመዘገበ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በ አቅም ማጎልበት፤ ትምህርት፤ ጤና፤ አካባቢ እንክብካቤ፤ ማህበራዊ ሃላፊነት መወጣት፤ ድህነት ቅነሳና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፤ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት፤ ዘርፎች ላይ በማተኮር አሳታፊ የሆኑና የተቀናጁ ፕሮጄክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 230 መጋቢት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚጫወቱ ወንድማማቾች

የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምርጥ ተጫዋቾችን...

ኢንፊኒቲ ለቤትና ለመኪና መግዣ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ...

የአዲሱ የወንጀል ህግ ስነ-ስርዓት የእርማት ስራዎች ሳይጠናቀቁ በሥራ ላይ እየዋለ ነው

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላለፉት 64 ዓመታት...

ናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኘ

​የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ ለመጀመሪያ...