ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት በማድረግ እያቀረበች የምትገኘው የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲያሳድር፤ ዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ አተኩራ መስራት እንደሚገባት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ባልተቃረነ መንገድ የባሕር በር የማግኘት መብቷን እንድትጠቀም ማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ጨምሮ፤ በሌሎችም ዲጂታል አማራጮች ሐሳቧን በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ማስረዳት አለባት” የሚሉት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው እና ፖለቲከኛው ጥላሁን ሊበን ናቸው።
የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ሕጋዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማሳካት የሁሉም ዜጋ ትብብር እንደምትፈልግ ያነሱት ዲፕሎማቱ፤ አዋጩ መንገድ ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንደሆነ አስምረውበታል።
“የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ተገቢ እና ወቅታዊና ነው” የሚል ሃሳብ ያላቸው አቶ ጥላሁን፤ “ዲፕሎማቶች፣ ማኅበራዊ አንቂዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ኤምባሲዎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ማኅበራዊ ሚድያውን በመጠቀም በተለያዩ ቋንቋዎች ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
የቀድሞ ዲፕሎማት ደያሞ ዳሌ በበኩላቸው፤ “የባሕር በር ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው የህልውና ጥያቄ ነው” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያቀረበች የምትገኘው የባሕር በር ጥያቄ፤ የባህር ላይ ንግድን በማሳለጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ፣ የመልማትና የመበልፀግ ፍትሃዊ ጥያቄ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ የሚገኘው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጀንዳ በመሆኑ፤ ዲጂታል ዲፕሎማሲን መከተል ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አንስተዋል።
የንግድ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የሰላም፣ የደህንነትና የተሰሚነት ጉዳዮች ከባሕር በር ባለቤትነት ጋር እንደሚገናኙ ያስታወሱት ዲፕሎማቱ፤ “ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በጋራ እንድትጠቀም የሚፈቅዱላትን ዓለም አቀፍ ሕጎች የቀጣናው አጀንዳ ማድረግ ይገባታል” ብለዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
