የቤተ ክርስቲያን ደውል አትናፍቁ!

Date:

በሀብታሙ ምናለ

ቤተክርስቲያን ከ“ለውጡ” ማግስት ጀምሮ በቤተክህነት ውስጥ እና በውጭ ሆኖ በተደራጀ ቡድን ያለ እረፍት እንደ በሶ ስትናጥ ከርማለች፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ቤተክርስቲያን ያልደረሰባት መከራ፣ እሳት ያልነካቸው ቤተ እምነቶች፣ የእምነቷም ተከታዮች ከቤት ንብረት ያልተፈናቀሉበት፣ ያልተገደሉባት፣ በጦርነት ሰላማቸውን ያላጡበት ወዴትም ቢኬድ የሀገራችን ክፍል የለም፡፡ ይሄን ሁሉ ችላ የተቀመጠች ቤተክርስቲያን አሁንም የሚደርስባት በደል መጠኑ እና መዋቅራዊ ጥቃቱ ባስ ብሎ መጥቷል፡፡

 የአሁኑ ከሌሎቹ ጊዜያት ለየት የሚያደርገው ከቤተ ክህነት እስከ ቤተመንግሥት የተዘረጋው የጥቃት መዋቅር በጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ፍንትው ብሎ በገሃድ በመውጣት ቤተክርስያኗ የተሸረበባትን የሴራ ድግስ እንድታውቅ ቢያረግም በንግግራቸው ድርድሩን አሜን ብላ እንድትቀበል፣ አንገቷን ደፍታ እንድትቀመጥ በግልጽ መስማት ተችሏል፡፡ – ቤተክርስቲያኗ ለእሷ ጥላቻ እና ንቀት ያለው መሪ በታሪኳ አጋጥሟት ያውቅ ይሆን?

ጠ/ሚር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ሚንስትሮቻቸውን እና ካቢኒያቸውን ሰብስበው ጥር 23/2015 ዓ.ም ማስታወሻ እያስወሰዱ “ስለ ሰላም እና ሰለ ሃይማኖት (ስለ ኦርቶዶክስ) ወቅታዊ ሁኔታ” በሰጡት ማብራሪያ ከዚህ በፊት ተናግሬዋለሁ ያሉትን ንግግር በማስታወስ አቋማቸውን ግልጽ ያደረጉበት ንግግር ትኩረቴን ስቦታል፡፡ “የደርግ መንግሥት ኃ/ሥላሴን የጣለው በኩዴታ ነው፡፡ ከዛም ደርግን በውስጥ ኩዴታ ለመጣል ጥረት ሁለት፣ ሦስቴ ያደረጉ ተብልተዋል፡፡ የመንግሥቱ ትልቁ ብቃት ኩዴታ ነው፤ በሚያውቀው ነገር ልትቀይረው አትችልም፡፡ ሲደረግ የመጣበትን መንገድ ስለሚያውቅ የሞከሩትን ቀረጣጥፎ በላቸው፡፡ ሕወሓት በሽምቅ ውጊያ መጣ፡፡ በሽምቅ ውጊያ ከመጣ በኋላ ይሄው እነ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እነ ቀጀላ መርዳሳ በሽምቅ ኢሕአዴግን እንጥላለን ብለው እዛው ቀሩ ኢሕአዴግ የመጣበት መንገድ ስለሆነ ኢሕአዴግን ማሸነፍ አይቻልም፡፡” – በረሃ ስንት ዓመት ተቀምጠው አንድ ስንዝር መሬት መያዝ እንዳልቻሉ፣ እጃቸውን እየጠቆሙ ስማቸውን ጠቅሰው ደጋግመው ሲናገሩ እነዚህ ሰዎች ዝምታን ለምን መረጡ? ለራሳቸው ክብር የላቸውም እንዴ? ብያለሁ፡፡ ጠቅላዩ ንግግራቸውን በመቀጠል፡-

“ወደ እኛ ደግሞ ሲመጣ በከተማ ውስጥ ብዙ ሙከራዎች እና በከተማ ውስጥ ግርግር ይታያሉ፡፡ በብልፅግና ውስጥ ሰው በመቅጠር ይሄ መንግሥት መቼም አይፈርስም እንዴት እንደሚሰራ እናውቀዋለን፤ እንዴት እንደሚረበሽ እናውቀዋለን፤ በዛ መንገድ የሚያስብ ካለ ራሱን ይበላ እንደሆነ እንጂ ለእኛ ችግር የለውም፡፡ ይሄ ነው አደገኛው ፖለቲካ” በማለት ብልፅግና የመጣበትን የአመፅ መንገድ ጠንቅቆ ስለሚያውቀው እርምጃችን የከፋ ይሆናል በማለት ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት በገዢው ፓርቲ ልሳን በሆኑ ሚዲያዎች በኩል አቋማቸውን ለቤተክህነት ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕዝብ ግልፅ አድርገዋል፡፡

ጠቅላዩ በቤተክርስቲያን የተፈጠረው ችግር ከድርድር ውጭ አማራጭ እንደሌለ ከዛ ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ መንግሥታቸው ታግሶ እንደማያልፍ ሲገልጹ ለተመለከተ ይህቺ ቤተክርስቲያን መከራዋ ገና ብዙ መሆኑን ተገንዝቦ ራስን ማበርታት እንዳለበት እንዲረዳ ያደርጋል፡፡  

ቤተክርስቲያን መብቷን ለማስከበር በእምነቱ አባቶች ፊት አውራሪነት የምታደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል የእምነቱ ተከታይ ምእመንም በደንብ ተናቦ ሊቀጥል እንደሚችል ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ገብቷቸዋል፡፡ ይሄ ተቃውሞ በዚህ መጠንና ርቀት ከቀጠለ የአራት ኪሎ መንበር እቶን እሳት ሆኖ እንደሚፈጃቸው ከመጡበት መንገድ አንጻር ያውቁታል፡፡ ስለዚህ የሰላም ሰባኪ ሆነው ፍላጎታቸውን ከተቻለ በንግግር ካልሆነም በኃይል ለማስፈጸም እንደሚጥሩ በግላጭ አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስም ጠቅላይ ሚንስትሩ ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት የሰጡትን ማብራሪያ በደንብ በመስማት ጠቅላዩ ስለ ቤተክርስቲያን የተናገሩት በሙሉ ሐሰት በመሆኑ እሳቸው እና መንግሥታቸው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አደብ እንዲገዙ የሚያደርግ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ካልሆነም ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ሁሉንም ያሳተፈ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ፤ የቤተክርስቲያን መብት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል መብቷን ለማስከበር ጥረት እንደሚደረግ የሚያሳውቅ ፈጣን የሆነ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡  

አንዳንድ ሰዎች “ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት ችግር ሲገጥማት የምታሰማውን ደውል ልትደውል፣ በመንግሥት የሚደርስባት መዋቅራዊ ጥቃት በቃ! ልትል ይገባል” በማለት ለሰማዕትንት ራሳቸውን አዘጋጅተው ጥሪዋን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ደረጃ የቤተክርስቲያንን ጥሪ የሚጠብቅ አካል/ትውልድ መፈጠሩ በራሱ መንግሥት እያደረገ ስላለው ስህተት ይቅርታ ጠይቆ የጠፋውን እርምት ለመውሰድ የሚያፋጥን ክስተት ነበር፡፡ ግን አሁንም መንግሥት ለመታረም ዝግጁ አይመስልም፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ የደረሰባትን በደል በይፋ በመናገሯ ብቻ ያስነሳውን ውጥንቅጥ እና መተራመስ ለተመለከተ የቤተክርስቲያን ደውል እንዲደወል በፍጹም አይፈልግም፡፡  

ቤተክርስቲያን ደውሏን ብታሰማ መብቷን ማስከበር ብቻ ሳይሆን ከሚመጣው ሀገራዊ ቀውስ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚለውጥ ክስተት ፈጥራ ልታልፍ ትችላለች፡፡ ይሄን ሁሉ በአንዴ ለመሸከም ሀገራችን የሚችል ጫንቃ አሁን ላይ የላትም፡፡ ሕዝቡንም ከገባበት ችግር የሚያወጣው አካል ስለሌለ ቤተክርስቲያንም ኃላፊነት ስለሚሰማት ይሄን ታደርገዋለች ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ “ሁለቱም ኃይሎች ጋር እውነት አለ” ብለው ያቀለሉት አካሄድ የእምነቱን ተከታዮች ከማስቆጣት አልፎ ቀጣይ ቤተክርስቲያኒቷ ከመንግሥት ጋር ሊኖራት ስለሚገባት ግንኙነት በደንብ እንድታጤነው እንዲያስገድዳት የሚያደርግ ነው፡፡ በመጀመሪያ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙት ሰዎች ጥያቄያቸው የቋንቋ ትምህርት ይስፋፋ ሳይሆን በግል ምቾት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ እየተሳተፉ አንስተውት የማያውቁትን ጥያቄ ሌሎች ሰዎች ባቀረቡት ላይ ተንተርሰው ቤተከርስቲያንን ለመከፋፈል ከዛም ባለፈ ቤተክርስቲያንን እና ምዕመናኑን አደጋ ላይ ለመጣል እየሄዱበት ያለው ርቀት ይቅርታቸውን ለመቀበል ዳገት እያደረገው ይገኛል፡፡ ይሄም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብቷን ልታስከበር ይገባል፡፡ – ደውሉ ግን ይቆያት፡፡

የቤተክርስቲያንን መብት ለማስከበር ከጾምና ጸሎት ባሻገር መደረግ ይገባቸዋል የምላቸው፡-

  • ቅዱስ ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶች ጉባዔ ጠርቶ ስለጉዳዩ በማስረዳት በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን ችግር በማስገንዘብ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንዲቆሙ እና የጋራ አቋም እንዲያወጡ ማድረግ፣
  • በቤተ ክርስቲያን ስር ያሉ ተቋማት ሰ/ት/ቤት አንድነት፣ ማኅበረ ቅዱሳን እና ወጣቶች እና ጎልማሶች ኅብረት የመሳሰሉትን በማናገር መብት የማስከበር ሂደቱ በአጭር ጊዜና ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲከናወን ማድረግ፣
  • ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ለሌላ እምነት ተከታዮችም ቢሆን ስለተፈጠረው ችግር በደንብ ማስረዳት፣
  • ምዕመናኑም ከቤተክርስቲያን አፈንግጠው የወጡ አካላትን በእምነት አባት ስም የሚደግፉ ግለሰቦች፣ ተቋማት ላይ ሰላማዊ የሆነ ቦይኮት ማድረግ (የእነሱን ምርት አለመጠቀም፣ የሥራ ውል ማቋረጥ፣ ከእነሱ ጋር ማንኛውንም ግንኙነት አለመድረግ)
  • ቤተክርስቲያን ስትጠቃ ዝም የሚሉ ችግሮቿን ደግሞ አጉልተው የሚያወጡ ሚዲያዎችን ሰው እንዳይከታተላቸው ማድረግ፣
  • በቤተክህነት ውስጥ በአንድም በሌላ ምክንያት አፈንጋጩን ቡድን የደገፉ፣ ለእነሱ ስልታዊ ድጋፍ የሚሰጡ ሠራተኞች ላልተወሰነ ጊዜ ከሥራም ሆነ ከደሞዝም ማገድ (አንዳንድ ግለሰቦች የጠሉትን መምቻ እንዳያረጉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል)
  • የብልፅግና ደጋፊ የሆኑ አማኞች ለቤተክርስቲያን ጥሪ ቅድሚያ ሰጥተው ትግሉን እንዲቀላቀሉ መጋበዝ፣
  • ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እና የፖለቲካ አላማ ያለው አካል በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳይኖረው በር መዝጋት፣ ትግሉ የሃይማኖት መብት ከማስከበር በዘለለ የፖለቲካ አላማ የሌለው መሆኑን በግልጽ ማሳወቅ፣
  • በኦሮሚያ ክልል ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የተፈጠረው ችግር እንዲረዳ በማንኛውም መንገድ እና የመገናኛ ብዙኃን በኩል በአፋን ኦሮሞ እንዲያውቀው ማድረግ፣
  • በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እስካሁን የደረሰው እና እየሆነ ያለውን ለውጭ ተቋማት እንዲያሳውቁ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ ማድረግ በሀገር ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ የመቀነስ እድሉ ከፍተኛ ሲሆን ገዢው ፓርቲ ግን በዛም በዚህ አቋሙ ከቀጠለ ቤተክርስቲያን የመጨረሻ ደውሏን ማሰማቷ የማይቀር እውነታ ነው፡፡

      እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ዕድገት ወደር የሌለው አስተዋጽኦ ላበረከተውና የሙዚቃው...

ሕወሓት ድብረጺዮንን የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጠ

የክልሉ ፕሬዚዳንት ተደርገው የተመረጡት  ድብርጺዮን ገ/ ሚካዔል (ዶ/ር)  ቃለ...

” ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች ” – ትራምፕ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ...

የአርበኞች ድል መታሰቢያ እና የዛሬው ትውልድ ለሕብረት ያለው አቋም

የጥንት ኢትዮጵያዊያንአርበኞች ድል 85 ኛው ዓመት መታሰቢያ ሚያዚያ...