የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፤ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ያስቆማል የተባለው፤ የትራምፕ እና ፑቲን ውይይት አለመሳካቱን ተከትሎ ወደ አሜሪካ ሊያቀኑ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ዘለንስኪ የፊታችን ሰኞ ወደ ዋሽንግተን በማቅናት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ትራምፕ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ጅምር ተስፋዎች አሉ ቢሉም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት መቆጠባቸው የኬይቭ ባለስልጣናትን ሳያስቆጣ እንዳልቀረ እየተነገረ ነው፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ስብስባ ዘለንስኪ ሊገኙ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ የሰላም ምልክቶች ግን ከኬይቭ ባለስጣልናት መምጣት እንዳለበት ለፎክስ ኒውስ ገልጸዋል፡፡
አሁን የሰላም ዋንጫ በዘለንስኪ እጅ ላይ ናት፤ አውሮፓውያንም በዚህ ሊሳተፉ ይችላሉ ዋናው ግን የዘለንስኪ ወደ ሰላም የመምጣት ፍላጎት ወሳኝ ነው ብለዋል ዶናልድ ጄ ትራምፕ፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም ከትራምፕ ጋር በሰሞነኛ ጉዳይ ላይ ለ90 ደቂቃ በሰልክ እንደተወያዩ፤ ረዥም እና ትርጉም ያለው ቆይታ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሰኞ ከትራምፕ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ እንገናኛለን፤ አስከፊውን ጦርነትም ለመጨረስም እንወያያለን፤ ስለተደረገልኝ ግብዣ በጣም አመሰግናለሁ ብለዋል ዘለንስኪ፡፡
የፊታችን ሰኞ ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬኑ አቻቸው ዘለንስኪ በዋሽግተን ተገናኝተው ከአላስካው የተለየ በምን አጀንዳ ላይ ሊያወሩ ይችላሉ የሚለው የሚጠበቅ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ሲቢሲ ፤ አልጀዚራ እና ዘ ናሽናል ዘግበውታል፡፡
