የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ኤምባሲዎች ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች አዲስ የተማሪ ቪዛ ቀጠሮ መስጠት እንዲያቆሙ ትእዛዝ አስተላልፏል።
በአሜሪካ ለመማር ያሚያመለክቱ ሰዎችን የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ በጥልቀት ለመፈተሽ በማሰብ አስተዳደሩ ይህን መመሪያ ማስተላለፉ ነው የተገለጸው።
የተፈረመው ይህ መመሪያ ለሁሉም የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች መላኩን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አስታውቀዋል።
መመሪያው የሀገሪቱ መንግስት በዓለም አቀፍ ተማሪዎች ላይ ከወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች አንዱ ሲሆን እነዚህ እርምጃዎች የተማሪ ቪዛን መሰረዝ እና የውጭ ተማሪዎች እንደ ሃርቫርድ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች እንዳይመዘገቡ መከልከልን ያካተታል።
የትራምፕ አስተዳደር መመሪያው የተላለፈው የሀገርን ደህንነት ለመጠበቅ እና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ነው ሲል ገልጿል።
በሌላ በኩል የዓለም አቀፍ መምህራን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ፋንታ አው “ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ስጋት አይደሉም” ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አክለውም መመሪያው ተማሪዎች ወደ አሜሪካ እንዳይመጡ ተስፋ ሊያስቆርጥ እና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የገንዘብ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አሳስበዋል ሲል ኤን.ቢ.ሲ ኒውስ ዘግቧል።
