በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ሴት ህፃናት ከልጅነት ጋብቻ ጋር በተያያዘ ለህልፈት እንደሚዳረጉ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የስነተዋልዶ ጤና ፣የቤተሰብ እቅድ፣የአፍላወጣቶችና ወጣቶች ፕሮግራም ሀላፊ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት የስነተዋልዶ ጤናን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዮ ስራዎች ተሰርተዋል።
ይህም የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለው የተገለፀ ሲሆን አሁን ላይ ከልጅነት እርግዝና ጋር በተገናኘ በርካታ ሴት ህፃናት ለህልፈት እንደሚዳረጉ ተጠቅሷል።
በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ እያሉ በጋብቻ በሚቆዮበት ወቅት ብዙ ቁጥር ያላቸውን ልጆች የመውለድ እድል ስላላቸው በወሊድ ጊዜ ለሞት ሊጋለጡ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ ተገልጿል።
ይህም አዲስ አበባን እና ድሬደዋን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች የሚታይ ነው ያሉት ሀላፊው በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር ቦታዎች ችግሩ በስፋት ይስተዋላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የልጅነት እርግዝናን ለመከላከል እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ የሚቆይ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
