የፖሊስ ኮሚሽኑ ለቀኩት ያለው ግለሰብ በስለላ፣ በህገወጥ መንገድ ድምበር አቋርጦ ወደ ሌላ ሀገር በመጓዝ፣ በሀገር ሉአላዊነት ላይ ጉዳት በማድረስ ብሎም በህዝብ መካከል ግጭትና አመፅ በማነሳሳት ድርጊቶች ነው።
የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከሳምንታት በፊት ከአንድ የኤርትራ መንግስት የፕሮፓጋንዳ ሰው (አወል ሰዒድ) ጋር በመገናኘት ቃለመጥይቅ የሰጠ ብርሃነ ገብረገርግስ ወይንም ደግሞ በማህበራዊ ትስስር መድረኮች በሚታወቅበት ስሙ “ልፍዓታይ ተስፋ” የተባለውን ግለሰብ በፍርድ ቤት ተእዛዝ መሰረት ሚያዝያ 29 ቀን በቁጥጥር ስር አውሎት የነበረ ቢሆንም ከአንድ ቀን በኃላ ሚያዝያ 30 ቀን የምርመራ ሂደቱን በማቋርጥ ከእስር ለቆታል።
የተጠርጣሪውን መለቀቅ ተከትሎ የፖሊስ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው መረጃም “የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ተቋማዊ ነፃነቱን ጠብቆ ምርመራ እንዳያከናውን ከአቅም በላይ የሆኑ ጫናዎች ደርሰውበታል ይህም ያልተፈለገ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ስለዚህ የምርመራ ሂደቱን በማቋረጥ በነፃ ለቀነዋል” ሲል አስታውቋል።

ይህን ተከትሎም በርካታ የትግራይ ተወላጆች በተፈጠረው ነገር የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለፅ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከህግ በላይ የሆነው አካል ማን ነው ኮሚሽኑ ከአቅም በላይ ጫና አሰደሩብኝ ያላቸው አካላት እነማን ናቸው ግልፅ ይደረግ ሲሉ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

ልፍዓተይ ተስፋ በመባል የሚታወቀው አክቲቪስት ከኤርትራ መንግስት የፕሮፓጋንዳ ሰው ከሆነው አወል ሰዒድ ጋር ያደረገው ቃለመጥይቅ ለእስሩ ምክንያት እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ቃለመጠይቁም በኤርትራ ምድር የተደረገ ስለመሆኑ ዳጉ ጆርናል ከምንጮቹ ሰምቷል።
