የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባካሄደው 12ኛው ዙር የውጭ ምንዛሪ ጨረታ፣ አንድ የአሜሪካን ዶላር በአማካይ 154.7 ብር የተሸጠ ሲሆን፣ በጨረታው የውጭ ምንዛሪ ድልድል ማግኘት የቻሉት የንግድ ባንኮች ቁጥር ቅናሽ አሳይቷል።
ብሔራዊ ባንኩ ታህሳስ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደዉ ጨረታው ለሽያጭ ያቀረበው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን 50 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ድልድል ያገኙት ባንኮች ቁጥር 13 ብቻ ነው።
ይህ ቁጥር ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው 11ኛው ዙር ጨረታ ድልድል ካገኙት 17 ባንኮች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር፣ የአራት ባንኮች ቅናሽ መታየቱ ተመላክቷል።
ከብሔራዊ ባንኩ ያገኘዉ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ዶላሩን በ154.7 ብር ለመግዛት ብቃቱን ያሟሉ ወይም ተቀባይነት ያለውን ዋጋ በማቅረብ ድልድል ያገኙት ባንኮች 13 ብቻ ናቸው።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሶሴሽን ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም በመጀመሪያው የሩብ ዓመት ውስጥ ብቻ በ8.1 በመቶ እንደተዳከመ መገለጹ ይታወቃል።
ከዚህም ባሻገር፣ በህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 11ኛዉ ዙር የውጪ ምንዛሪ ጨረታ ለአንድ የአሜሪካን ዶላር አማካይ የምንዛሪ ተመን ብር 154.39 ሆኖ መመዝገቡ የሚታወስ ነው። ይህም ከሁለት ወራት በፊት በ9ኛው ዙር ጨረታ ከተመዘገበው አማካይ ተመን ጋር ሲነፃፀር፣ የዶላር ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር የ11.72% የምንዛሪ ተመን ጭማሪ ታይቷል።
ካፒታል ጋዜጣ
