አርቲስት ሰላማዊት ደስታ ባደረባት ህመም ምክንያት በህክምና ስትረዳ ቆይታ ግንቦት 21/2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፋለች።
የአርቲስት ሰላማዊት ደስታ የሽኝት ፕሮግራም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግንቦት 22/2018 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ቤተሰቦቿ፣ ዘመዶቿ፣ ጓደኞቿና የሙያ አጋሮቿ በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን የቀብር ስነስርአቱ ከቀኑ 7:00 ሰዓት በማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
የተወዳጇ አርቲስት ሰላማዊት ደስታ አጭር የህይወት ታሪክ
አርቲስት ሰላማዊት ደስታ ከአባቷ ከአቶ ደስታ አድማሱ እና ከእናቷ ከወ/ሮ ፀሐይ ብርሃኑ አዲስ አበባ ከተማ የካቲት 7/1967 ዓ.ም የተወለደች ሲሆን ትምህርቷን ባልቻ አባ ነፍሶ አንደኛ ደረጃ እና አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1-12ኛ ክፍል ተምራ አጠናቃለች። እንዲሁም ትምህርቷን አጠናክራ በመቀጠል ከአልፋ ኮሌጅ በሴክሬተሪ ሙያ ዲፕሎማ ተመርቃለች።
አርቲስት ሰላማዊት ደስታ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ታሪክ ውስጥ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ብቅ ያለች ድንቅ ተዋናይት ስትሆን ከ1987-1989 ዓ.ም በቴአትር እድገት ክበብ (ፋዘር ቤት) ለሁለት ዓመታት የቴአትር ስልጠና ወስዳ የጥበቡን ዓለም በይፋ ከተቀላቀለች በኋላ ከወጋገን ኮሌጅ በቴአትር ዲፕሎማ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በማታው መርኃ-ግብር በቴአትር ጥበብ ሙያ በ2013 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቃ በኢትዮጵያ የጥበብ ገፅ ላይ የበኩሏን አሻራ ማኖር የቻለች ሁለገብ አርቲስት ነበረች።
አርቲስት ሰላማዊት ደስታ በርካታ የቴአትር ፣ የቴሌቪዥን ድራማና ፊልሞች ላይ በመተወን ድንቅ ብቃቷን ያስመሰከረች የጥበብ ባለሟል ነበረች። ከ1987 ዓ.ም ህይወቷ እስካለፈበት ግንቦት 21/2018 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ቴአትር ቤቶች በርካታ የጥበብ ስራዎችን ሰርታለች።
- በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ከመቀጠሯ በፊት አባ ጉጉ ፣ ጫጩት፣ ታሚ፣ ፓፔት፣ ዛኪ የተሰኙ የህፃናት ቴአትሮች ላይ በትወና ተሳትፋለች።
- መጋቢት 1/1990 ዓ.ም በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት በኮንትራት ተቀጥራ – የቀበሮ ባህታዊና ሁለተኛው የቁንጅና ውድድርን በትወና እንዲሁም ተንኮሉ የተሰኘውን ቴአትር በማዘጋጀትና በትወና በመሳተፍ ችሎታዋን አሳይታበታለች።
- ከግንቦት 1/1991 – ጥር 2/1994 ዓ.ም በራስ ቴአትር ቤት ቋሚ ቅጥር በመሆን የሰራች ሲሆን – ዘር አዳኝ የተሰኘው ቴአትር ላይ በትወና ተሳትፋለች።
- ከጥር 3/1994 – ጥቅምት 30/1996 ዓ.ም ድረስ ወደ ህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ተዛውራ በሙያዋ አገልግላለች።
- ከህዳር 1/1996 ዓ.ም ጀምሮ ህይወቷ እስካለፈበት ግንቦት 21/2018 ዓ.ም ድረስ በራስ ቴአትር ቤት ተዛውራ ስታገለግል ቆይታለች።
አርቲስት ሰላማዊት ደስታ ባጋጠማት ህመም ሳቢያ በህክምና ስትረዳ ቆይታ በተወለደች በ51 ዓመቷ ግንቦት 21/2018 ዓ.ም ከዚህ አለም ድካም አርፋለች።
የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በአርቲስት ሰላማዊት ደስታ ህልፈተ-ሄይወት ምክንያት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ እግዚአብሔር ነፍሷን በመዓዛ ገነት እንዲያሳርፍና ለቤተሰቦቿ፣ ዘመድ፣ ወዳጆቿ፣ ጓደኞቿና የስራ ባልደረቦቿ ልባዊ መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን።
የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት-ኮምኒኬሽን
