በአውስትራሊያ መቀመጫውን ያደረገዉ ግዙፉ አስካሪ ሜታልስ የተባለ የማዕድን አሳሽ ኩባንያ በአፍሪካ ያለውን የፍለጋ እንቅስቃሴውን ወደ ኢትዮጵያ በማስፋፋት ሪፍት ቫሊ ሜታልስ የተባለውን የግል ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ለመግዛት ስምምነት ላይ መድረሱን በይፋ አስታውቋል።
ሪፍት ቫሊ ሜታልስ በደቡባዊ ኢትዮጵያ በሚገኘው በአዶላ አካባቢ አምስት ትላልቅ የወርቅ ፕሮጀክቶች ባለቤት ሲሆን፣ ይህ ስምምነት አስካሪ ሜታልስ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን ሳካሮ፣ ሳካሮ ምዕራብ፣ ሌጋ ደምቢ ደቡብ፣ ሜጋዶ እና ዋዩ ቦዳ የተባሉትን 460 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ፕሮጀክቶች እንዲያገኝ አስችሎታል።
ይህ ስምምነት አስካሪ ሜታልስ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅና የመዳብ ክምችት በሚገኝበት ክልል ውስጥ ስልታዊ የሆነ ቀዳሚ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችለው ሲሆን፣ ለዚህም የመጀመሪያ ክፍያ 200,000 የአሜሪካ ዶላር በጥሬ ገንዘብ እና 200,000 የአሜሪካ ዶላር በአስካሪ የአክሲዮን ድርሻ እንዲሁም የፍለጋው ውጤት በሚታይበት ደረጃ የሚከፈል ተጨማሪ ክፍያዎችን እንደሚያካትት ተገልጿል።
ይህ ግዙፉ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ መግባት በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የማዕድን ፍለጋ አሻራ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሰፋ ስልታዊ እርምጃ እንደሆነ ታምኖበታል።
CapitalNews
