በአማራ ክልል ከሞጣ ወደ አዴት የሚወስደው ዋና መንገድ ከሳምንት በላይ በመዘጋቱ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተከስቷል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው የገረገራ ቀበሌና የአዴት ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከሞጣ ወደ አዴት የሚወስደው መንገድ ከ10 ቀን በላይ በመዘጋቱ በተለይ ጤፍ ለመዝራት ጉልጓሎ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች የሚያስፈልጋቸውን የአፈር ማዳበሪያ በኩንታል እስከ 14 ሺህ ብር በጥቁር ገበያ ለመግዛት ተገደዋል ብለዋል።
በይልማና ዴንሳ ወረዳ ግምብ አስቴሮ ቀበሌ ” ቆሎ መሻጫ ” ተብሎ በሚጠራ ጎጥ የሚኖሩ አርሶ አደር አያሌው በላቸው በቆሎ፣ በርበሬና ጤፍ ዘርተው ማዳበሪያ እያፈላለጉ እንደሆነ ይናገራሉ።
” ይህ ወቅት ጤፍ ዘርተን ጉልጓሎ የምናደርግበት ነበር፤ በጉልጓሎ ወቅት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋል፤ መንገዱ በመዘጋቱ ምክንያት ማዳበሪያ እየገባ አይደለም ” በማለት ” ነጋዴ አንድ ኩንታል ማዳበሪያ በ14 ሺ ብር በጥቁር ገበያ እየሸጠልን ነው ” ሲሉ አስረድተዋል።
” እኔን ጨምሮ ሌሎች አርሶ አደሮች ይሁን ብለን ለመግዛት ብንሄደም ‘ ጨርሰናል ‘ ብለዋል ዋጋው ቢጨምርም ወቅቱ ከሚያልፍብን ብለን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርን እየፈለግን ነው ” ብለዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከወቅቱ ጋር ተያይዞ ችግሩ በአርሶ አደሮች ላይ በረታ እንጂ ከመንገዱ መዘጋት ጋር ተያይዞ በአካባቢው በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እየታየ ነው በአንፃሩ ደግሞ የግብርና ምርቶችን አርሶ አደሩ ተዘዋዉሮ ባለመሸጡ በርካሽ እንዲሸጥ አስገድዶታል ብለዋል።
ለለቅሶ፣ ዘመድ ለመጠየቅ እና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቀበሌዎች መሄድ ፈልገው ትራንስፓርት ያጡ ሰዎች በእግራቸው እየተንቀሳቀሱ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል።
መስመሩ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሞጣ ወደ ባህር ዳር እና ሌሎች አካባቢዎች የሚወስድ ዋና መንገድ በመሆኑ ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍሰት የሚታይበት ነው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ባሕር ዳር
