አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፤ ቀይ ባህር ደግሞ መውጫ መግቢያዋ ሆኖ ወደ ነባራዊ እውነታው ሊመለስ ይገባል ሲሉ የአፋር የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፋር የሀገር ሽማግሌዎች፣ አሰብ የኢትዮጵያ አካሏ፤ ቀይ ባህር ደግሞ መግቢያ መውጫ በሯ ሆኖ ለዘመናት ስለማገልገሉ በታሪክ የተዘመገበና ዓለም የሚያውቀው ሃቅ መሆኑን አንስተዋል።
የአፋር ክልል ህዝብ ደግሞ ቀይ ባህር አቅራቢያው እያለ የተቆለፈበትና ከባህሩ የተገለለ ሆኖ በፍጹም ሊኖር የማይገባ በመሆኑ መብቱ ሊከበርለት ግድ ይላል ሲሉ አንስተዋል።
ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ጅብሪል ዓሊና አቶ ኡስማን ኢብራሂም፤ ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ከሚገኘው ቀይ ባህር ተነጥላ ፈፅሞ ልትቀጥል አይገባም ብለዋል። በመሆኑም አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፤ ቀይ ባህር ደግሞ መውጫ መግቢያዋ ሆኖ ወደ ነባራዊ እውነታው ሊመለስ ይገባል ነው ያሉት።
በየትኛውም መመዘኛ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከቀይ ባህር መነጠል አይገባም በማለት አፅንኦት ሰጥተው፤ ለመብታችን መከበር ህጋዊና መሰረታዊ ጥያቄያችን ይቀጥላል ብለዋል፤ የሀገር ሽማግሌዎቹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጋራ ከመጠቀምም ባለፈ የህይወትና የደህንነት ጉዳይ በመሆኑ የግድ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ኡስማን ተናግረዋል።
ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ መሐመድ ሰኢድ፤ የአሰብና የቀይ ባህር ጉዳይ ታሪካዊና ህጋዊ መብታችን ሆኖ ሳለ በዝምታ መኖራችን ሁላችንንም ያስቆጨ ነው ብለዋል። አሁን ላይ ግን ትክክለኛ ምላሽ የሚሻ የሀገር ህልውና እና የትውልድ ጥያቄ በመሆኑ በአፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
