የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከተቋቋመበት ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በድምሩ 6.5 ቢሊዮን ብር ካሣ መክፈሉን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ ይህን ያሳወቀው 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ባስናወቀበት ወቅት ነው።
ይህ ካሣ የተከፈለው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት ለሆኑት ለኢነርጂ፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለግንባታዎች፣ ለአቪየሽን፣ ለከባድና ቀላል ፋብሪካዎች፣ ለፋይናንስ ተቋማት እና ለንግዱ ማህበረሰብ በንብረት፣ በሕይወትና በሕጋዊ ኃላፊነት ላይ ለደረሱ ጉዳቶች ሲሆን፣ ዜጎች ያለሥጋት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።
መድን ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 12.8 ትሪሊዮን ብር የሚገመት የመድን ሽፋን ለደንበኞቹ የሰጠ ሲሆን፣ አገልግሎቱን በብቸኝነት ሲሰጥ በነበረባቸው 19 ዓመታትም የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ እና ዝርዝር የመድን ውለታዎችን (policy wording) በመስጠት ለግል የመድን ኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባለፉት 50 ዓመታት ያስመዘገባቸው የእድገት ውጤቶች ከምሥረታ ጊዜው ጋር ሲነፃፀሩ ጉልህ መሻሻል ያሳያሉ ተብሏል።
በዚህም መሰረት ፤ ጠቅላላ የተከፈለ ጉዳት ካሣ ከ17.6 ሚሊዮን ብር ወደ 6.5 ቢሊዮን ብር ሲያድግ፣ ከታክስ በፊት የነበረው ትርፍ ደግሞ ከ10.4 ሚሊየን ብር ወደ 1.98 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
ጠቅላላ ሃብቱ ደግሞ ከ77.4 ሚሊየን ብር ወደ 24.3 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ የውሎች ብዛት ከ17,320 ወደ 170,479 መድረሱን አስታወቀ።
የመድን ድርጅቱ በአፍሪካ አስመጪና ላኪ ባንክና በኢትዮ ሪ ኢንሹራንስ አ.ማ.ን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳትፎ ያለው ሲሆን፣ የማህበራዊ ግዴታውንም በጤና፣ በትምህርት እና በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። ከህዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም. መከበር የጀመረዉ የድርጅቱ 50ኛው ዓመት ክብረ በዓል ለተከታታይ ሁለት ከግማሽ እንደሚቆይ ተጠቁሟል።
