34 አገራትን በአባልነት ያቀፈው የዓለም ፕሬስ ካውንስሎች ማሕበር (WORLD ASSOCIATION OF PRESS COUNCILS (WAPC)) በቅርቡ በኬኒያ ናይሮቢ ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትን የአባልነት ጥያቄን ተቀብሎ ማፅደቁ ታወቀ፡፡
መቀመጫውን ተርኪዬ ስታንቡል ያደረገው የዓለም ፕሬስ ካውንስል ዓመታዊ ጉባኤውን በተለያዩ አባል ሀገራት የሚያከናውን ሲሆን የፕሬስ ነፃነት ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በጋራ ለመከላከልና ነፃና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በየሀገራቱ እንዲገነባ የሚሰራ ተቋም ነው፤ በናይሮቢው ጉባኤ ከኢትዮጵያ ሌላ የሩዋንዳንና የሶማሊያ ሚዲያ ካውንስሎችን የአባልነት ጥያቄ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡
የዓለም ፕሬስ ካውንስል ፕሬዝዳንትና የታንዛንያ ፕሬስ ካውንስል ሰብሳቢ የሆኑት ሚስተር ዴቪድ ኦማዮንጎ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የWAPC አባልነት ከአፍሪካ ባሻገር እንዲስፋፋ ያለውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፣ ከጋዜጠኞች ለሰብአዊ መብቶች ካናዳ (JHR)፣ ከአለም አቀፍ የጋዜጠኞች ፌደሬሽን (IFJ) እና ከድንበር አልባ ዘጋቢዎች ድርጅት ጨምሮ ከአለም አቀፍ የጋዜጠኞች ድርጅቶች ጋር እየተካሄዱ ያሉ ተግባራትን በዝርዝር አመላክተዋል።
ዓላማው በአለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የመግባቢያ ሰነዶችን (MOUs) ማጠናቀቅ እና ከሌሎች አህጉራት በተለይም ከአውሮፓ አባላትን መሳብ ሲሆን ይህ ደግሞ ማህበሩ የገንዘብ እና የቴክኒክ ሀብቶችን ማሰባሰብ እና ማንቀሳቀስ እንዲችል ያስችለዋል ብለዋል።
WAPC ራሱን ለአለም አቀፍ የፕሬስ ካውንስል ምርምር ማዕከል አድርጎ የማቆም ዓላማ እንዳለው የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ተቆጣጣሪ አካላትን፣ የሚዲያ ኢንዱስትሪውን እና የሲቪል ማህበረሰብን የሚያሰባስብ አካል እንደመሆኑ፣ መንግስታት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚዲያ ተቋማትን የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስርዓት እንዲደግፉና እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምክር ቤቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ላይ የታዛቢነት ወንበር እንዲሰጠው እንደሚጠይቅ በጉባኤው መዝጊያ ላይ ተመልክቷል፡፡
