የተለያዩ መፅሐፍት የደረሱትና ለ8 ዓመት በህክምና ሙያ ያገለገሉት ዶክተር ደሳለው ካሳ ጠፋ የሚባለው መፅሐፈ ሄኖክ ላይ የሚያተኩር “ፓሌሮዳ” የሚል መፅሐፍ ለንባብ ማብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡
“’አንድ ጠቃሚ የሆነ መፅሐፍ ከሀገር ወጥቷል፤ መፅሐፉ ቢገኝ ለሀገሪቱ ታላቅ መነሳት ይሆናል፤ በተለይ በህክምና ግኝት ትልቅ እምርታ ያመጣል፤ የምዕራባውያን የሕክምና ቴክኖሎጅ የሚቀዳው ከዚያ መፅሐፍ ነው’” የሚለው አፈታሪካዊ ንግግር መፅሐፉን ለመድረስ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡
“ለመጻፍ ያነሳሳኝ የኢትዮጵያ ድርሳናት የመዘረፍ ጉዳይ ነው” ያሉት ደራሲው፣ “በሺዎች የሚቆጠሩ ብራናዎች ምዕራባውን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አሉ” ብለዋል። ብዛታቸውንም ወደ 9 ሺሕ አድርሰውታል።
“ወደ 4 ሺሕ የሚሆኑትን ምዕራባውያኑ አምነው ደርድረዋቸዋል፡፡ ሌሎቹ ግን ከመጋረጃ ጀርባ በተለያዬ መንገድ ያሉ ናቸው፡፡ የጠፉት ድርሳናት ሃይማኖታዊ ብቻ አይደሉም፤ አብዛኛዎቹ ከፍተኛ መገለጥን ቢጠይቁም የህክምና ምስጢራትን የያዙ ናቸው” ብለዋል፡፡
ከእነዚህም የመፅፈ ሔኖክ ብራናዎች እንደሚገኙበትና ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ድብቅ ጥበብም እንደያዙ ጠቅሰው፣ በዚሁ መነሻ በመፅሐፈ ሔኖክ የሚያጠነጥን “ፓሌሮዳ” የተሰኘውን መፅሐፍ መፃፋቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠፋውና ስውር ጥበብ የያዘው እውነተኛው መፅሐፈ ሔኖክ አለመገኘቱ እንደ ሀገርም፣ እንደ ትውልድም አሳሳቢ መሆኑን መፅሐፉ በጥልቅ እንደሚያስረዳ አመልክተዋል፡፡
“የጠፋ መፅሐፍ በእርግጥም እንዳለ፣ ተገኘ ተብሎ ተተርጉሞ ያለው መፅሐፍ ሔኖክ ብቻ እንዳልሆነ ከራሱ ከመጽሐፉ ፍንጮችን አግንቻለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
ስለብራና መፅሐፍቱ ጥቅም ደራሲው ምን አሉ?
እነዚህን የብራና መፅሐፍት ከውጭ ሀገራት ማስመለስ ቢቻል ኢትዮጵያ የገባችበትን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት እንደሚያስችል ገልጸው፣ “ዓለም ለሺሕ ዓመታት የሰራቸውን ቴክኖሎጅዎች ሁሉ በ10 ዓመታት መስራት ያስችላሉ” ነው ያሉት።
“ማንኛውም ሰው የሔኖክ ብራናዎችን መጥፋት ከልቡ ቢያይ እንቅልፍ የሚያስተኛ አይደል” የሚሉት ዶክተር ደሳለው፣ ይህም ለመጻፍ ያነሳሳቸውና መፅሐፍቱ ወደሀገር እንዲመለሱ አሳስበዋል።
“መፅሐፈ ሔኖክ የሃይማኖት እሳቤዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያስቀምጣል፡፡ ንድፈ ሀሳቦቹን አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን በትምህርት ኳሪኩለም ቀርጸው ይማሩባቸዋል። ግን የድሮ አባቶቻችን ያለፉበት መንገድ ነው” ይላሉ ደራሲው።
የመፅሐፉ ስያሜ፣ ጭብጥና ግጭት ምንድን ነው?
መፅሐፉ፣ “ፓሌሮዳ” የሚል ስያሜ ተስጥቶታል፡፡ ስያሜውም “ፓሊሲፒታ፣ ሌሴፖስ፣ ሮፒልታ እና ዳሔር የሚባሉ የጠፉ አራቱን ብራና የሄኖክ መፅሐፍት የያዘ ምህጻረ ቃል ነው” ብለዋል፡፡
“ፓሌሮዳ” አራቱ የሔኖክ መፅሐፍት ላይ የሚያጠነጥንና ልብወለዱ አሁን ያለውን የሔኖክ መፅሐፍ ፍች የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በልብወለዱ ውስጥ የሔኖክ መፅሐፍን ፍለጋ የተነሱ የኢትዮጵያ ምሁራን “አብርሆት” የሚል ቡድን መስርተው ከኢትዮጵያ ገዳማት እስከ አውሮፓ ድብቅ የዋሻ ላይብራሪዎችን በማሰስ በሚያደርጉት ፍለጋ ላይ የልብወለድ ግጭቱን አድርጓል፡፡
ስውር ምስጢር የያዙ የብራና መፅሐፍት ከምዕራዊያን እጅ ማስመለስ፣ መፅሐፍቶቹ ቢገኙ ምዕራባውያኑ ያለፉበት ሥልጣኔ ከመከተል ይልቅ ከራሳችን አልፈን ለዓለም እንደምንተርፍ እውነታውን ፍንትው አድርጎ ማሳየት የመፅሐፉ ጭብጥ ነው፡፡
#TikvahEthiopia
የኢትዮጵያ ብራናዎች አብዛኛዎቹ የህክምና ምስጢራትን የያዙ ናቸው
Date:
