ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)
ግዮን መጽሔት :- እግር ኳስ ዳኝነት በሀገራቸን እንዴት እንደገባና ማን እንዳመጣው በሠነድ የተቀመጠ መረጃ ባይኖርም፤ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስን በሚያውቁት፣ በሚስማሙበትና በመሰላቸው ሕግ ይዳኙ እንደ ነበር እግር ኳስ በሀገራችን ሲጀመር የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ። ተጋጣሚዎች ስላሉ እነርሱን ለመዳኘት የግድ ሰው ስለሚያስፈልግ፤ ማጫወት በእግር ኳስ ውስጥ ዋነኛው ክፍል ነበር።
በተፈሪ መኮንንና በምኒልክ ት/ቤት ውስጥ ከውጭ የመጡ መምህራን ለተማሪዎቻቸው በሀገራቸው እግር ኳስ በምን መንገድ እንደሚዳኝ ስላስተማሯቸው፤ ተማሪዎቹ በሰፈራቸው ሲጫወቱ የቀሰሙትን ትምህርት ወደ ተግባር በመቀየር ሙያውን ለማስፋፋት ተሞክሯል። ከውጭ መምህራን ትምህርቱን ከማግኘታቸው በፊት፣ ኢትዮጵያውያን በመሰላቸው የዳኝነት ሕግ ይጠቀሙ ነበር። ይሄ ባህላዊ ዳኝነት ይባላል፡፡
ምስክር
በኋላ ደግሞ ዘመናዊና ባህላዊ (ሀገርኛ) ዳኝነት እየተባለ ይሠራበት ነበር። ይሄም መላው ዓለም የሚተዳደርበት ሕግ ወደ ሀገራችን ሲገባ ቀድሞ ይሠራበት የነበረው ሕግ እየተቀረ ሄደ። ሆኖም በአንዳንድ ቦታዎች በስምምነት በቀድሞው ሕግ ይሠራ ነበር። በ1920ዎቹ መግቢያ አካባቢ በየሰፈሩ ያሉ ወጣቶች ተመራርጠው ሲጫወቱ የሚመደበው ዳኛ ከሜዳው ዳር ሆኖ ነበር የሚያጫውተው። ያን ጊዜ መጠሪያው ‹‹አልቢትር›› ሳይሆን፣ ስሙ ‹‹ምስክር›› የሚል ነበር፤ ያየውን እንዲመሰክር ይደረግ ነበርና።
የምስክር አብዛኛው ሥራ ጎል ሲቆጠር፣ ጥልፊያ ሲፈጸም ወዘተ. ምስክርነት መስጠት ነበር። ጎሉ አጨቃጫቂ ከሆነ መግባት አለመግባቱን ይመሰክራል። ምስክርነቱንም በመሀላ ያረጋግጣል። በመሀላ የተረጋገጠው ምስክርነት የመጨረሻ ውሳኔ ነበር። በኋላ ግን የውጭ ሀገር መምህራን በስዕል ካሳዩዋቸው በኋላ፣ ዳኞች ውጭ ሳይሆን ሜዳ ውስጥ ገብተው እየተሯሯጡ መሥራት እንዲችሉ ተደረገ። ኳስ ከመስመር አልፋ ስትወጣ የእጅ ውርወራ ሳይሆን በእግር የሚጀመር ሲሆን፤ ጀማሪው ባለ ሜዳው እንዲሆን ተደርጓል። ኳሷ ማንም ነክቷት ትውጣ፣ የባለ ክልሉ ቡድን ኳሱን መስመር ላይ አድርጎ እንዲጀምር ይደረግ ነበር።
ያኔ በዳኝነት የሚመረጥ ሰው በባሕርዪው ምስጉንና የማይዋሽ ነው። ጨዋታውን ለመምራት ድምጽን በተመለከተ የመቻል ክለብ መሥራችና የመጀመሪያው የብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ የነበሩት አቶ ዓመለወርቅ ተክለዜና እንዲህ በሚል ያስታውሳሉ፡- ‹‹… ሰፈራችን የነበሩ ልጆች ሲጫወቱ ትንሽ ሆኜ አስታውሳለሁ። ዳኛ ተብለው የሚመደቡት ጣታቸውን አፋቸው ውስጥ ከተው በመንፋት በፉጨት ያስቆማሉ። በኋላ ግን ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ግጥሚያ ሲደረግ አልቢትሩ በጡሩምባ ሲያጫውት አስታውሳለሁ። ነገር ግን የአራዳ ዘበኛ ከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጭ ጡሩምባ የሚነፉትን ስለከለከለ ይሄ ነገር ቀረ። በጣሊያን ጊዜ እኔ ለስድስት ኪሎ ቡድን ስጫወት አልቢትሮች በፊሽካ ማጫወት ጀመሩ። ያም ቢሆን ለነጮቹ ብቻ ነበር በብዛት የሚፈቀደው›› ይላሉ።
ዳኛ ‹‹ምስክር›› በሚባልበት ጊዜ በስምምነት ከሚሠራባቸው ሀገርኛ ሕጎች ውስጥ ለቀስተኛ ሬሳ ይዞ ሲያልፍ ጨዋታው ይቆማል፤ የሃይማኖት አባቶች፣ ባላባቶችና በመንደሩ የተከበሩ ሰዎች ሲያልፉ ይቋረጣል። እነርሱ ርቀው ከሄዱ በኋላ ጨዋታው ከቆመበት ይጀምራል። ተጫዋቾች ቢደባደቡ ከሜዳ እንዲባረሩ አይደረግም፤ ‹‹ምስክር›› ያስታርቃቸውና ተመልሰው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የግብጾች ያለመተማመን
በ1920ዎቹ መጀመሪያ ‹‹ምስክር›› ከዳር ወደ መሀል ሲገባ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሰው ሜዳውን ሙሉ መሸፈን ይቸግረዋል በሚል ሁለት ምስክር ተመድቦ ጨዋታው እንዲካሄድ ተደረገ። አንደኛው ምስክር ግማሹን ሜዳ፣ ሌላኛው ደግሞ የቀረውን ሜዳ ሸፍነው እንዲያጫውቱ ይደረግ ነበር። ዘመናዊ ዳኝነት መጥቶ በአንድ አልቢትር ውድድር ሲመራ፣ አንዳንድ ቦታ ሁለት ዳኛ (ባህላዊ ወይም ሀገራዊ አሠራር ይሉታል) ይጠቀሙ ነበር። በተፈሪ መኮንንና በምኒልክ ት/ቤት ያስተምሩ የነበሩ የውጭ ሀገር መምህራን፤ ግቢ ውስጥ በሚደረግ የተማሪዎች ግጥሚያ ስሕተት ሲፈጸምና ክርክር ሲነሳ፣ ‹‹ሕጉ እንዲህ ነው›› እያሉ በማስረዳት ዘመናዊ ዳኝነትን አብረው ከኳሱ ጋር በማስተማራቸው ት/ቤቶች የዳኝነት እውቀት ማዳበሪያ እስከ መሆን ደርሰው ነበር።
በ1927 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ የመጣው የፈረንሳይ መርከበኞች ቡድን በግጥሚያው እለት ተፈጸመ የተባለውን የዳኝነት ስሕተት መነሻ በማድረግ፤ የእግር ኳስ ሕጎችን በማስተማርና በፈረንሳይኛ በመጻፍ፣ በወረቀት ላይ የሰፈሩት ሕጎች እንደ ገዢ የእግር ኳስ ሕግ ተወስደው በየሰፈሩ ለሚገኙ ተጫዋቾች ሁሉ እንዲታደል ተደረገ፤ እናም በዚያ ይተዳደሩ ነበር። አንዳንድ አሻሚ ነገሮች ሲኖሩ አስተርጓሚ እየተፈለገ የፈረንሳይኛው ጽሑፍ ወደ አማርኛ እየተቀየረ መተዳደሪያ እስከ መሆን ተደርሶም ነበር።
ነገሮች በዚህ ቀጥለው፤ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን በ1936 ዓ.ም ሲጀመር አካራካሪው ነገር ሕጉ ነበር። የጨዋታው አብዛኛው ጊዜ፣ ‹‹… ጠልፈሃል አልጠለፍኩም፤ ነክተሃል አልነካሁም፤ ኳሱ ወጥቷል አልወጣም …›› በሚሉ ክርክሮች ይባክን ነበር። ተመልካቹ ጊዜውን የሚያጠፋው፣ ‹‹… ልክ ነው፤ ልክ አይደለም›› በሚል ጭቅጭቅ በመሆኑ አንዳንዱ ከጨዋታው ይልቅ በሜዳው ላይ የሚደረገው ሙግት ያስደስተው ነበር። የኃላ ኋላ በልማዳዊ ሕግ መሥራቱ ቀርቶ ዳኞች ዘመናዊ ትምህርት መውሰድ አለባቸው ተብሎ ታመነበት።
የመጀመሪያውን የዳኝነት ትምህርት በሕጋዊነት የሰጡት ሚ/ር ፒየር ኮንቲ የተባሉ ጣሊያናዊ ሲሆኑ፣ ጊዜውም በ1941 ዓ.ም ነበር። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከመጀመሪያዎቹ ኮርስ ተካፋዮች አንዱ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለኮንቲ አስተርጓሚ በመሆን ጭምር ሠርተዋል። ያን ጊዜ ፌዴሬሽኑ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ተላቆ እራሱን ችሎ መንቀሳቀስ የጀመረበት ጊዜ በመሆኑ ዳኞችን አስተምሮና ያስተማራቸውንም ሕጋዊ አድርጎ ለጨዋታ ደረጃ እየሰጠ እንዲዳኙ ያደርግ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጭ ሀገር አዲስ አበባ በመምጣት የዳኙት ግብጻዊው እስማኤል ካሌብ ሲሆኑ፣ ጊዜውም በ1942 ዓ.ም ነበር። ሰውዬው ወደ ሀገራችን መጥተው ዘመናዊ ዳኝነት እንዴት እንደሆነና ከእኛ ጋር ያላቸው ልዩነት ምን ያህል እንደነበር አሳይተዋል። እርሳቸው እንዲመጡ ወጪውን የቻሉት የግሪክ ኮሚኒቲ ሲሆን፣ የተጋጠሙት ሄሊኒካ የተባለው የግብጽ ቡድንና የአዲስ አበባ ምርጥ ነበሩ።
የሀገራችን ዳኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊፋ ያዘጋጀውን የኢንተርናሽናል ዳኝነት ኮርስ የወሰዱት ዘግይቶ ነበር። ኮርሱን የሰጡት ዩጎዝላቪያዊው ፕሮፌሰር አንድሪየቪች ነበሩ። የዳኞች አለባበስን በተመለከተ ከጅማሬው ነጭ ጨርቅ (ገበርዲን) ጭንቅላታቸው ላይ አስረው ይገቡ ነበር። ከዚያም ልብስ ተጀመረ። በ1950ዎቹ ጥቁር ሸሚዝ ይለብሱ ጀመር። ጥቁሩ ልብስ እስከ 1986 መጨረሻ ሄዶ በ1987 ማንኛውም ቀለም ያለው ልብስ እየተሠራበት ይገኛል። ረዳት ዳኞች በኋለኛው ዘመን ኮታቸውን አውልቀው እንደማራገቢያ ይጠቀሙ ነበር። በ1950ዎቹ መጀመሪያ የዳኛ እጥረት ስለነበር ከስታዲየም ውጭ ያሉት አንዳንድ ውድድሮች ያለ ረዳት ዳኛ ይካሄዱ ነበር። አንዳንድ ዳኞች ይሄ ሁኔታ ይመቻቸው እንደ ነበር ይናገራሉ፤ ውሳኔ ለመስጠት ይመቻል ይላሉ።
ዳኝነት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለውና ስስ ነገር እንደሆነ ከብዙ ነገር ማየት ይቻለል። አሸናፊም ተሸናፊም ዳኛን መውቀሳቸው አይቀርም። ተሸናፊ ቡድን ዳኛን ከጥቃቅን ነገር ጀምሮ ለሽንፈቱ ምክንያት አድርጎ ያቀርባል። አሸናፊም ቢሆን 1 ለ 0 ረትቶ ‹‹ዳኛው ያችን ግብ ባይሽርብን ኖሮ 2 ለ 0 አሸንፈን ነበር ብሎ ይወቅሳል። ዳኝነት ምሰጋና የሌለው ነገር እንደሆነ ብዙዎቹ አልቢትሮች ሲናገሩ ይደመጣል። አንዳንድ ቦታ ማሸነፍን ከማስቀደም በመነሳት በአልቢትሮች ላይ እምነት የማጣት ሁኔታ እስከ መታየት ደርሷል። ግብጽ ውስጥ የእግር ኳስ ዳኝነትን በተመለከ ሁሌም ውዝግብ ይነሳል። በተለይ ዛማሌክና አል-አህሊ ሲጫወቱ በሀገር ውስጥ ዳኛ እምነት በማጣታቸው ከጣሊያን ያስመጡ ነበር።
በወቅቱ ይሄን የተመለከቱት የካፍ ፕሬዝዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ‹‹ሞትን የመሰለ ነገር በፍርድ ቤት በሀገራቸው ሰው እየተዳኙ ለእግር ኳስ ግን በሀገራቸው ዳኛ እምነት አልጣሉም›› ብለው ተናግረው ነበር። ይሄ የሚያሳየው ሙያው ከባድና ውስብስብ በመሆኑ ነበር። የሚገርመው ከጣሊያን የመጡት ዳኞች ከወቀሳ አላመለጡም። ኮንቲ የተባለ ኢጣሊያዊ ዳኛ አበሳውን አይቶ ነበር የሄደው። ብዙ ጊዜ ከጣሊያን አስመጥተው መፍትሔ በማጣታቸው ተመልሰው በሀገራቸው ዳኛ ሁለቱን ቡድኖች ለማጫወት ተገደዋል።
የቢንጎ ዳኛ
ዳኛ ሰው ነው። እንደማንኛው የሜዳ ላይ ተዋናይ ይሳሳታል። እንኳ ሌላው ቀርቶ በዳኝነት የአንድ ቡድን ሁለት ደጋፊዎች ውሳኔውን ትክክል ነው አይደለም በማለት እስከ መከራከር የሚደርሱበት ጊዜ አለ። ብዙዎቹ ተጫዋቾችና አሠልጣኞች ባመጡት ውጤት ተጠያቂ ላለመሆን ዳኛን ምክንያት አድርገው በተለያየ ጊዜ ያቀርባሉ። በዳኝነት ላይ ብዙ ወቀሳ ስለሚቀርብ ፊፋ ዳኛው ባየው ነገር እንዲወስን መብት ሰጥቶታል። በአንድ ወቀት አቶ ይድነቃቸው በዳኝነት ላይ የሚቀርበውን ወቀሳ በመመልከት፣ ‹‹… ዳኝነትን ከነስሕተቱ መቀበል አለብን። በሜዳ ላይ ተጫዋች እንደሚሳሰተው ሁሉ እነርሱም የጨዋታው አካል ናቸው›› ብለው ነበር።
ዳኛ ሲሳሳት ይቀጣል። ከጨዋታ ምደባ መከልከል አንስቶ በወርና በዓመታት ደረጃ እርምጃ ይወሰድበታል። ዳኛን በአግባቡ የሚተቹ እንዳሉ ሁሉ፣ በስሜታዊነት የሚቃወሙም አልጠፉም። አንድ አልቢትር እንዲህ ብሎ ነበር፣ ‹‹… በእረፍት ጊዜዬ ቢንጎ የመጫወት ልማድ ነበረኝ። የማዘወትረው መብራት ኃይል ግቢ ውስጥ ነው። የቢንጎ ዳኛው በድምጽ ማጉያ ሕጉንና የጨዋታውን ዓይነት ይናገርና ጨዋታው ይቀጥላል። ዳኛው ማሽኑ የነገረውን ነው ለተጫዋቾቹ የሚያሳውቀው። እንደዚያም ሆኖ ውጤቱ ያልቀናቸው ሰዎች ዳኛውን ሰድበው የመጫወቻውን ካርድ በንዴት መሬት ወርውረው ከዚያም ሲብስ ሰባብረው ሲሄዱ በተደጋጋሚ አያለሁ። ይሄን ጊዜ በእግር ኳስ ሜዳ ፉክክር ባለበት ቦታ ብዙ ሰዎች በስሜት እንደሚቃወሙ በመረዳቴ ሜዳ ላይ በትንሽ ስሕተት ሲያወግዙኝና ሲናገሩኝ በትዕግሥት ለማለፍ እንድችል ረድቶኛል። የቢንጎ ዳኛ ራሱ የሚወስነው ምንም ነገር የለም። የማሽኑን ብቻ ነው የሚናገረው። የኳስ ዳኛ ግን በቀይ ያስወጣል፤ ጎል ይሽራል፤ ስሕተት ሲኖር ሪጎሬ ይሰጣል። ስለዚህ ተመልካቹ ከማሸነፍና መሸነፍ ጋር ስሜታዊ ስለሚሆን ቁጣ ውስጥ ሲገባ መቀበል የግድ ነው። እኔም ዳኝነቱን ከዚህ አንጻር አየዋለሁ›› ብሏል፡፡
በአንድ ወቅት አንድ አልቢትር መብራት ኃይልና እርሻን ሲያጫውት ሁለተኛ ቅጣት ምት ሰጠ። ሌላ ሰው ሳይነካለት ተጫዋቹ በቀጥታ መትቶ አገባ። ዳኛው መሻር ነበረበት። ግን አጸደቀ። የመብራት ተጫዋቾች አልተከራከሩም። ተመልካቹም አልተቃወመም። ሳያውቁ ቀርቶ ሳይሆን ሁሉም ረስቶታል ወይም ቅጣቱ ሲሰጥ በአንድ ሰው ብቻ መመታቱን አላስተዋሉም። መብራት በዚህች ግብ ተሸንፎ ወጣ። በሚዲያ ዳኛው ያለምንም ስሕተት አጫውተው እንደወጡ ተነገረ። በሌላ ጊዜ ይሄው ዳኛ ከመልስ ምት በርቀት የተመታ ኳስ አጥቂው አግኝቶ ሲያገባ ግቡን ሻረው አጸደቀ። ረዳቱ ባንድራ አንስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ በመልስ ምት ኦፍሳይድ አልነበረም። ተመልካቹ የመሀል ዳኛውን ለምን ትሽራለህ ብሎ ተቃወመው። ዳኛው በትክክል አጫውቶ ሲበጠብጥ እንደዋለ ተደርጎ በተመልካቹና በሚዲያው ተወገዘ። ዳኛው የተሳሳተውን ትክክል ነው ብለው ተቀበሉት። ትክክል የነበረውን ደግሞ ተሳስተሃል ብለው አወገዙት።
በሜዳ ላይ ተቃውሞው ከሕጉ አንጻር ሳይሆን ከስሜታዊነት እንደሆነ እነዚህ ሁኔታዎች በቂ አመላካች ናቸው። ዳኛ እንደማንኛው ሰው ይሳሳታል። የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው ተካበ ዘውዴ አንድ ነገር ያስታውሳል፡- ‹‹… በ1977 ዓ.ም ናይሮቢ ላይ ከኬንያ ቡድን ጋር ስንጫወት ከርቀት የተመታ ኳስ ብረቱን መትቶ እኔ ፊት ነጠረ። ዳኛው በቅርበት አልነበረም። ሩቅ ሆኖ ገብቷል ብሎ ወሰነ። በዚህች ኳስ ተሸንፈን ወጣን። ከሁለት ዓመት በኋላ በ1979 ዓ.ም ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ አበባ ላይ ከታንዛንያ ጋር ስንጫወት አንድ ኳስ አጥቂው ሲመታ እኔ ለመያዝ ስሄድ አዳለጠኝና ሳልደርስ ቀረሁ። ልጁ ኳሱን አጥብቆ ስለመታው መረቡም በጣም ስለተወጠረ ኳሱ መረቡን ነክቶ ሲመጣ ቶሎ ቀለብኩና ለጋሁት። ዳኛው ጎል እንዳልገባ አምኖ አስቀጠለ። ልጁ ግብ ነው ብሎ ሲከራከር ዳኛው ቢጫ ሰጠው። የእኛም ተጫዋቾች መግባቱን አላወቁም። መግባቱን የምናውቀው እኔና ልጁ ብቻ ነን። ኬንያ ላይ ጎሉ ሳይገባ ጸደቀ። አዲስ አበባ ላይ ገብቶ አልገባም ተባለ። ዳኛ ባየው ነገር እንደሚወስን ከዚያ በኋላ ተረዳሁ›› ይላል፡፡
የኤለትሪክ አልቢትር
ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የካቲት 19 ቀን 1952 ዓ.ም በታተመው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ስለአልቢትሮች እንዲህ የሚል አስተያየት ጽፎ ነበር፡- ‹‹… ጥሩ ዳኛ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ … ሰዎች ይሳሳታሉ። በየሳምንቱ አልቢትሮቻችን በትንሽም ስሕተት ቢሆን ስድብ አሰልችቷቸዋል፡፡ ተጫዋቹ ካልደበደብናችሁ ይላል። ተመልካቹ በስድብና በዛቻ ጠምዷቸዋል። በዚህ አኳኋን ለመጪው ዓመት አልቢትር የሚገኝ አይመስለኝም። ስለዚህ ያለው አማራጭ በኤሌክትሪክ የሚሠራ አልቢትር ሳያስፈልግ አይቀርም። ሊቃውንቶች በሬድዮ ኃይል የሚሠራ የኤሌትሪክ አልቢትር ይሠራሉ ብለን እንጠብቃለን። የኤለትሪክ አልቢትር ተሠርቶ ለተመልካቹ ሙሉ ደስታ ሳይሰጥ ሲቀር ‹ባልቦላው ትክክል አይደለም፤ ኮንታክት ሆኖ ነው› መባሉ አይቀርም›› በሚል ተመልካቹ ከዳኞች ጋር ያለውን አመለካከት አስፍሯል፡፡
——————
ማስታወሻ፡- ይኽ ጽሑፍ ተወዳጁ ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) የግዮን መጽሔት ታላቅ እህት ለነበረችው ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት አዘጋጅቶት የነበረና በወቅቱ (2006 ዓ.ም) መጽሔቷ በመታገዷ ምክንያት የሕትመት ብርሃን አግኝቶ ለንባብ ሳይበቃ የቀረ ነው፡፡ የጽሑፉን ቀጣይ ክፍል በሚቀጥለው ዕትም ይጠብቁ፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 229 የካቲት 2018 ዓ.ም
