ግዮን መጽሔት :- ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከምንም በላይ የምትፈልገው አቀራራቢ፣ አስተዋይና ሰላምን የሚሰብኩ መሪዎችን ነው፡፡ በመሆኑም ዕጩዎችን ስንመዝን ለሚከተሉት እሴቶች ያላቸውን ቅርበት ማጤን ይኖርብናል፦
- አካታችነት (Inclusivity)፦ ዕጩው የሚያራምደው ሐሳብ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በእኩልነት የሚያይ ነው? ወይንስ በአግላይነትና በልዩነት ላይ የተመሠረተ?
- ለሰላም ያለው ዝንባሌ፦ በንግግሮቹ ውስጥ ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን የሚዘሩ ወይንም ሌላውን ወገን የሚያንኳስሱ ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ? ሰላም ወዳድ መራጭ፣ ሰላም ወዳድ መሪን መምረጥ አለበት፡፡
- የመደራደርና የመስማማት ብቃት፦ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ልዩነቶች በውይይት ይፈታሉ፡፡ ዕጩው ከማይስማማቸው ወገኖች ጋር ተቀምጦ ለመነጋገርና የጋራ መፍትሔ ለማምጣት ያለው ዝግጁነት ሊፈተሽ ይገባል፡፡
- የወጣቱ ሚና፦ ከደጋፊነት ወደ መርማሪነት
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የዚህ ምርጫ ትልቁ ሞተር ናችሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ወጣቶች ለፖለቲካ ፓርቲዎች በጭብጨባ፣ በፉጨትና በሰልፍ ሞቅታ የታጀበ ድጋፍ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ አሁን ግን ያ ጊዜ ማለፍ አለበት፡፡
ወጣቱ አሁን መጠየቅ ያለበት ‹‹ይህ ዕጩ ለወጣቱ የሥራ ዕድል፣ ለትምህርት ጥራትና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ምን ይዞልኛል?›› ብሎ ነው፡፡ በጭፍን ደጋፊነት (Blind Support) የሚሰጥ ድምፅ የዴሞክራሲ ጠንቅ ነው፡፡- ወጣቱ በእያንዳንዱ የምርጫ ክርክር ላይ በመገኘት፣ በሰለጠነ መንገድ ጥያቄዎችን በመሰንዘር እና የዕጩዎችን ብቃት በመፈተሽ የአገሪቱን የፖለቲካ ባሕል ማዘመን ይኖርበታል፡፡
ማጠቃለያ፦ የእርስዎ ድምፅ የእርስዎ ኑሮ ነው
ውድ መራጮች፤
የምርጫ ካርድ መያዝ ማለት የሥልጣን ባለቤት መሆን ማለት ነው፡፡ ይህ ሥልጣን ደግሞ በጥንቃቄ ካልተያዘ አደጋ አለው፡፡ ምርጫ አንድ ቀን ነው፤ ውጤቱ ግን ለዓመታት ይከተለናል፡፡ የምንሰጠው ድምፅ የልጆቻችንን ትምህርት ቤት፣ የአገራችንን ሰላም፣ የኑሮ ውድነታችንን እና የፍትሕ ሥርዓታችንን ይወስናል፡፡
ስለዚህ፦- የፓርቲዎችን መርሐ-ግብር (Manifesto) አንብቡ፡፡
- በዕጩዎች መካከል የሚደረጉ ክርክሮችን አድምጡ፡፡
- ከጎረቤቶቻችሁና ከጓደኞቻችሁ ጋር በሐሳብ ላይ ተወያዩ፡፡
- በመጨረሻም፣ ለኅሊናችሁና ለአገራችሁ የሚበጀውን በምክንያታዊነት መርጡ፡፡
በምርጫ ካርዳችሁ ላይ የምታርፈው ምልክት፣ የነገዋን ኢትዮጵያ መልክ የምትስል ብዕር መሆኑን አትዘንጉ፡፡ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ (Informed Decision) በመስጠት፣ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለዘላቂ ሰላም የበኩላችንን እንወጣ፡፡
ብልህ መራጭ፣ ብቁ መሪ፣ የበለፀገች አገር!
ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን (Youth and Cultural Development Foun
dation – YCDF) ከአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማዕከል (ECES) ጋር በመተባበር ነው።
የወጣቶች እና ባህል ልማት ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት፣ ባህላዊ እሴቶችን በማሳደግ፣ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በማስፋፋት እና የወጣቶችን ንቁ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሠራ ገለልተኛ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ግንዛቤ በመፍጠርና አቅማቸውን በማጎልበት የላቀ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 233 ግንቦት 2018 ዓ.ም
