ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን የገለጹት “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ቃል ትናንት በተካሄደው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ መረጃን እንደ ሀብት በመቁጠር የምንገለገልበት ዋና ምክንያት “ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባትም የዳታ ወይም የመረጃ፣ የምግብ፣ የፖሊሲ እና ሌሎችም ሉዓላዊነቶች መረጋገጥ እንዳለባቸውና እንደሚያስፈልጉም አስገንዝበዋል።
ጉዳዩን ሲያብራሩም የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ መረጃን (ዳታን) በመግዛት አልያም በመዋስ ማረጋገጥ እንደማይቻል አንስተዋል።
በውሰት መረጃ የሚቀረጸው ፖሊሲ በተሟላ መንገድ የሀገርን ፍላጎት፣ ጥያቄና ሕልም ሊያሳካ የሚችል እንዳልሆነም አስረድተዋል። ስለሆነም የራስን መረጃ በተለያዩ የመረጃ ማዕከላት ውስጥ ማሰባሰብና ማጠቃለል መቻል ለፖሊሲ ሉዓላዊነት ትልቅ ግብዓት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ያለን ሀብትና አቅም በሌሎች አካላት የሚገለጽ ከሆነ፣ ትክክለኛውን ደረጃና ግምገማ በሙሉ ልብ ለማወቅ አዳጋች ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እንዲሁም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ላለፉት በርካታ ወራት የሰበሰቧቸው መረጃዎች ለኢትዮጵያ የቀጣይ ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት ይህ መድረክ ከግንቦት 10 ቀን ጀምሮ የተካሄደ መሆኑ ታውቋል።
