የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት “ለታክስ”፣ “ለቀረጥ” እና “ለአካባቢ ልማት” በሚል ሽፋን በየሰፈሩና በመንገድ ዳር የተቋቋሙ ሕገ-ወጥ ኬላዎች በሙሉ እንዲነሱ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።
የክልሉ መንግሥት ትናንት አርብ ህዳር 5/2018 ዓ.ም በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ በየአካባቢው ተቋቁመው ነፃ የምርት ዝውውርን የሚያደናቅፉ ሕገ-ወጥ ኬላዎች ምርት በነፃነትና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለገበያ እንዳይቀርብ በማድረግ፣ ዜጎች በሥራቸዉ ልክ እንዳይጠቀሙ እንቅፋት መፍጠራቸውን ገልጿል።
ቀደም ሲል በሀገር አቀፍ ደረጃ ነጻ የምርት ዝዉዉርን የሚገቱ በየአካባቢዉ የተቋቋሙ ኬላዎች እንዲነሱ መንግስት ውሳኔ ማሳለፉን ያስታወሰው የክልሉ መንግስት መግለጫ፤ ይሁን እንጂ ውሳኔው በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ወጥ በሆነ መንገድ እየተተገበረ አለመሆኑን ገልጧል።
ይህ መዘግየት በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል ያለው መግለጫው፤ ይህንን ኢኮኖሚን የሚያዳክም አሰራር ሙሉ በሙሉ ለማስቆም፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት “ለታክስ”፣ “ለቀረጥ” እና “ለአከባቢ ልማት” በሚል ሽፋን በየሰፈሩና በመንገድ ዳር የተቋቋሙ ሕገ-ወጥ ኬላዎች በሙሉ መነሳት እንዳለባቸዉ ወስኗል ብሏል።
በዚህም የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እና ለጸጥታ ሥራ አጋዥነት በሚታወቅ የክልሉ ወይም የፌዴራል አካል ተፈቅደው፣ በግልጽ አሰራር የሚመሩ ኬላዎች ብቻ ተግባራቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል ሲል ጠቁሟል።
