” የግል ትምህርት ተቋማትን ስጋት ላይ የጣለው አዲሱ መመሪያ ምን ይላል ” በሚለው ከዚህ ቀደም በቀረበው ዘገባችን፣ የዘርፉ ተዋናዮችን ቅሬታዎች አቅርበናል፡፡
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ደግሞ ለቅሬታዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ፣ በሰጡት ቃለመጠይቅ፣ በትምህርት ተቋማቱ የዳግመ ምዝገባና የመስክ ምልከታው የሚታዩት ዋና ዋና የሚባሉት መስፈርቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የትምህርት ተቋማቱ፣ ትውልድን ለማስተማር በትንሹ ምን ማሟላት አለባቸው የሚለውን ነው የምናየው በማለትም ተናግረዋል፡፡
አቶ ውብሸት ታደለ በዝርዝር ምን መለሱ ?
” አንድ የትምህርት ተቋም ስናስብ የራሱ የሆነ ድባብ ሊኖረው ይገባል፡፡ አንዳንዶቹ ተቋማት የሆነ ህንፃ ላይ አንድና ሁለት ወለል ብቻ ተከራይተው ከቡቲኩና ከካፌው ጋር እየተጋፉ ነው የሚሰሩት፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ የኮሌጅነት ቅርፅ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ መስፈርቶች መቀመጥ አለባቸው፡፡ ግን ደግሞ የተቀመጡትን ሁሉንም መስፈርቶች በሙሉ እንተግብር አላልንም፡፡ በጣም መሰረታዊ የሚባሉትን ብቻ እንዲያሟሉ ነው እያደረግን ያለነው፡፡ በጣም በዝቅተኛ መስፈርት ነው እየተመዘኑ ያሉት፡፡ እነዚህን ዝቅተኛ መስፈርቶችስ ምን ያህሎቹ ተቋማት ያሟላሉ የሚለውን ደግሞ ሪፖርቱ ሲለቀቅ የምናየው ይሆናል፡፡
መስፈርቶቹ ምንድናቸው ካልን አንደኛው የመማሪያ ህንፃን የሚመለከት ነው፡፡ ከአምስት ፕሮግራሞች በላይ ያላቸው ተቋማት የራሳቸው ግቢና ህንፃ እንዲኖራቸው ተደንግጓል፡፡ ተከራይተውም ቢሆን፣ የራሳቸው ግቢና ህንፃ ይኑራቸው፣ ከሌሎች የንግድ ስራዎች ጋር ሊዳበሉ አይገባም ነው፣ ይህ አንድ መሰረታዊ መስፈርት ነው፡፡
ግን ደግሞ በአብዛኞቹ ኮሌጆች ዘንድ መስፈርቶቹን ለማሟላት ስለሚቸገሩ ለድርድር እያቀረብናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ከአምስት ፕሮግራሞች በታች የሚሰጡ ጀማሪ ባለሀብቶች፣ የራሳቸው ህንፃና ግቢ እንዲኖራቸው አናስገድድም፡፡ እነሱ ከሌሎች ቢዝነሶች ጋር ተዳብለው መስራት ይችላሉ ብለናል፣ እስኪጠናከሩ ድረስ፡፡ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድተን ነው በዚህ ደረጃ መስፈርቱን አውርደን እየሰራን ያለነው፡፡ መስፈርቶቹ በምንም መልኩ ሊሟሉና ሊተገበሩ አይችሉም የሚባሉ አይደሉም፡፡
ሁለተኛው መስፈርት ለማስያዣነት የሚያስቀምጡት ገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ መቼ ገብተው መቼ እንደሚወጡ አይታወቅም ነበር፡፡ በተለይም አወጣጣቸው ስርዓት ስላልነበረው፣ መቼ እንደወጡ እንኳን ማወቅ አይቻልም ነበር፡፡ ይህን ስርዓት ለማስያዝ ነው 500 ሺህ ብር ማስያዣ እንዲያስቀምጡ የጠደነገገው፡፡ ከእንግዲህ፣ ማንኛውም ተቋም ከገበያው ሲወጣ፣ አወጣጡ ስርዓት ያለው ይሆናል፣ የጠራ መረጃም ይኖረናል ማለት ነው፡፡
ሶስተኛው መስፈርት የሰው ሀይሉን የሚመለከት ነው፡፡ ከበፊቱ መመሪያ ብዙም የተጨመረ ነገር የለውም፡፡ አንድ ነገር ነው ብቻ ነው ያሻሻልነው፡፡ የማስተርስ ተማሪ ፒኤችዲ ዲግሪ በሌለው ረዳት ፕሮፌሰር መሰልጠን የለበትም የሚል ነው፡፡ የአስተማሪው የትምህርት ደረጃ ከሚያሰለጥነው የትምህርት ደረጃ አንድ እርከን ከፍ ይበል ነው፡፡ ለምሳሌ የዲግሪ ተማሪ ማስተርስ ዲግሪ በያዘ መምህር፣ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪ ደግሞ የዶክትሬት/ፒኤችዲ ዲግሪ ባለው መምህር መሰልጠን አለባቸው፡፡ አሁን ግን ፒኤችዲ ዲግሪ ሳይኖራቸው ረዳት ፕሮፌሰር የሚል ማዕረግ ያላቸው አስተማሪዎች ናቸው ከነሱ ጋር አቻ የሆነን የማስተርስ ዲግሪ ስልጠና የሚሰጡት፡፡ ማስተርን በማስተር ማለት ነው፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም ብለናል በመስፈርቱ፡፡
ከዚያ ውጭ፣ በግል ኮሌጆች ድጋፍ ሰጪ ሰራተኛውም፣ የአስተዳደር ሐላፊዎችም ፒኤችዲ ዲግሪ ይኑራቸው አልተባለም፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ዲኖቻቸው/ የተቋማቱ ሐላፊዎች እንኳን ፒኤችዲ ከሌላቸው ብለን ጥብቅ ቁጥጥር አናደርግም፣ እውነት ለመናገር፡፡ ትኩረታችን አስተማሪዎቹና ትምህርቱ ላይ ነው፡፡ በሒደት ደግሞ ወደ ስታንዳርዱ እናስገባቸዋለን የሚል እሳቤ ነው ያለን፡፡
አራተኛው መስፈርት መምህራንን መዋዋስ በተመለከተ ነው፡፡ ሁሉንም ትምህርቶች በትርፍ ሰዓት/ፓርታይም መምህር አታስተምሩ ነው እንጂ ሁሉም አስተማሪዎቻችሁ የሙሉ ሰዓት ተቀጣሪዎች/ፉልታይም መምህራን ይሁኑ አላልንም፡፡ ትምህርት ብዙ ማንበብ፣ መጣርና ማማከር የሚያስፈልገው፣ የምርምር ስራ የሚያስፈልገው ስራ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ስራ የሆነች ሰዓት ላይ ብቻ አስተምሮ በሚሔድ በትርፍ ሰዓት ብቻ በሚሰራ መምህር ልታስኬደው አትችልም፡፡ መምህሩ ሶስት አራት ቦታ ላይ ከተጠመደ እንዴት ነው የምርምር ስራውን የሚሰራውና የሚያሰራው፡፡ የተወሰኑ የራሳችሁ ቋሚ መምህራን ይኑሩዋችሁ፣ ሌሎችን ደግሞ በፓርታይም መምህራን መሸፈን ትችላላችሁ ነው ያልነው፡፡
አምስተኛው መስፈርት፣ አንድ ተቋም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ቢያንስ 25 በመቶ ካላሳለፈ ይዘጋል የሚል ነው፡፡ አንድ ተቋም አራት አመት ካስተማራቸው 100 ተማሪዎች ቢያንስ 25ቱን ማሳለፍ ካልቻለ መዘጋት ነው ያለበት፡፡ ተማሪዎችን ካላሳለፈ እኮ እያስተማረ አይደለም፣ የሀገር ሀብት እያባከነ ነው ያለው፡፡
አራት አመት ሙሉ ካስተማራቸው ተማሪዎች 75 ከመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ከወደቁ፣ ያንን ሁሉ ሀብት ያባከነው ለምንም ነው ማለት ነው፡፡ ያ ተቋም ለምን ይቀጥላል፡፡እንዳይዘጋ ከፈለገ በደንብ አሰልጥኖ ተማሪዎቹን አብቅቶ የመውጫ ፈተናን ማሳለፍ ነው ያለበት፡፡ እንደገና ደግሞ 25 በመቶ ካላሳለፈ የሚባለው በኮሌጅ ደረጃ ሳይሆን በፕሮግራም ደረጃ ነው፡፡ ለምሳሌ 25 በመቶ ያላሳለፈው የአካውንቲን ትምህርት ከሆነ፣ ያ ትምህርት ነው የሚዘጋው እንጂ ተቋሙ አይደለም የሚዘጋው፡፡
ይህንን አሰራር ደግሞ በአንዴ ተግብሩ አላልንም፡፡ የእፎይታ ጊዜ ሰጥተናቸዋል፡፡ ይህ አሰራር የሚተገበረው መመሪያው በፀደቀበት በ 2015 ዓ.ም ትምህርት በጀመሩ ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ ያኔ አንደኛ አመት የነበሩ ተማሪዎች በ 2019 ዓ.ም የሚመረቁ ናቸው፣ በነዚህ ላይ ህጉ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ድንገት ተነስተን ዘንድሮ ቢያንስ 25 በመቶ አስመርቅ አላልንም፡፡ ለ 2019 ዓ.ም ካስተማርካቸው ተማሪዎች 25 በመቶውን ለማሳለፍ ተዘጋጅ ብሎ የቤት ስራ መስጠት የተጋነነ አይደለም፡፡ “
@tikvahethiopia
