ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጎንደር ቃል-ኪዳን ቤተሰብ መርሃ-ግብር አማካኝነት በዘንድሮው ዓመት ብቻ 28 የደቡብ ሱዳን እና የሶማሊያ ተማሪዎችን ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ጋር እየኖሩ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስተሳሰሩን አስታውቋል።
በመርሃ-ግብሩ ከ2012 እስከ 2018 ዓ.ም. ድረስ ለ7 ተከታታይ ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች በርካታ ተማሪዎችን ከቤተሰቦች ጋር በማስተሳሰር ተማሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩና እንዲማሩ እድል መፍጠሩን ተንግረዋል፡፡
የጎንደር ቃል-ኪዳን ቤተሰብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ወልደገብርኤል እንደገለጹት፤ መርሃ-ግብሩ ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ከቤተሰቦች ጋር አስተሳስሯል።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የባዕድነት ስሜት እንዳይሰማቸው እና ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ መርሃ-ግብሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ መርሃ-ግብሩን ለማስፋት ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርዓት፣ የተወሰነ የስራ መዋቅር፣ በቂ በጀት እና የተቀናጀ የዩኒቨርሲቲና የከተማ አመራር ትብብር እንደሚያስፈልግ ኃላፊው አስገንዘብተዋል።
በሰላም ሚኒስቴር በኩል የጎንደር ቃል-ኪዳን ቤተሰብን ተሞክሮ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋት ባለሙያዎችን በመመደብ እና ተቋማትን በመደገፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተመላክቷል።
