“የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ውስጥ ነው” ሲል

Date:

ህወሓት “መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት እየጣሰና እያኮሰሰ ነው” ሲል በመክሰስ ስምምነቱ “ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቋል” ሲል አስጠነቀቀ።

ህወሓት ሐሙስ ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የፌደራል መንግሥት በትግራይ የተደረገውን ጦርነት ለማስቆም የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ቁልፍ ድንጋጌዎች ለመተግበር አልቻለም” ሲል ገልጿል።

ቡድኑ በመግለጫው “የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይን አካባቢዎች ተቆጣጥረው የሚገኙ ኃይሎችን በመደገፍና በማስታጠቅ እንዲሁም የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በማደናቀፍ ስምምነቱን ትርጉም አልባ ለማድረግ እየሰራ ነው” ሲል ከሷል።

መግለጫው አክለውም፥ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ዓላማው ዘላቂ የጦርነት ማቆም እንዲመጣ፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲሁም ለፍትሕ፣ ለመልሶ ግንባታና ለፖለቲካ ውይይት መሠረት ለመጣል ነው ብሏል።

ይሁን እንጂ “የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም ያለው” ህወሓት፣ “አዲስ አበባ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በገባችው ስምምነት ላይ ጣልቃ ገብታለች” ሲል ከሷል።

መግለጫው አያይዞም “በወረራ በተያዙ አከባቢዎች የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች በማንነታቸው የተነሳ አፈና እና ግድያ እየተፈፀመባቸው መሆኑን” ገልጾ “የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች በብርድ፣ በበሽታ፣ በረሃብ እና በቸልተኝነት እየሞቱ እንደሆነም” ጠቅሷል።

ህወሓት በመግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በፓርላማ ያደረጉት ንግግር ላይ ትችት ሰንዝሯል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ፊት ቀርበው በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት የሁለት ወር ግጭት በማለት መግለጻቸው በክልሉ ለአምስት ዓመታት የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማቃለል ነው” ብሏል። ይህም “በትግራይ ሕዝብ ሞትና ስቃይ ላይ መቀለድ እና ላጠፉት ጥፋት ንስሐ አለመግባታቸውን ያሳያል” ሲል መግለጫው አስረድቷል።

መግለጫው አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈናቃዮች ወደየቤታቸው ከመመለሳቸው ይልቅ ሕዝበ ውሳኔን ማስቀደማቸውን በመተቸት፣ “መንግሥት የትግራይን ምድርና ሕዝብ የስነ-ሕዝብ አወቃቀር ለመቀየር እየሰራ ነው” ሲል ከሷል።

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች በትግራይ ሕዝብና ተቋማት ላይ ሲያሰራጩት የነበረው ስም ማጥፋትና ማስፈራራት ቀጣይነት አካል ነው” ሲል መግለጫው አመልክቷል።

በተጨማሪም “የኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ ዙር ጦርነት የማስነሳት አደጋ በሁሉም ረገድ ከባድ መሆኑን በመግለፅ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ” አሳስቧል።

መግለጫው በመጨረሻም፣ “የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ አካል በአስቸኳይ ለስብሰባ በመቀመጥ አሁን ያለውን ሁኔታ እንዲገመግምና አደጋ ላይ ያለውን ስምምነት እንዲያድን” ጠይቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህወሓትን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ባለማክበር እንዲሁም ከፌዴራል የሚላክ በጀትን ለልማት ሥራዎች ከማዋል ይልቅ ለወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በማዋል መወንጀላቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ ትናንት ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ መንግስታቸው “በትግራይ ክልል ውስጥ ተጨማሪ ውጊያ እንደማይፈልግ” ተናግረዋል። አክለውም የመንግስታቸው ትኩረት አገሪቱን በጋራ በማልማት ላይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

“መንግሥትን በኃይል የመጣል ማንኛውም ሙከራ ፈጽሞ እንደማይሳካ” የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ አያይዘውም በትግራይ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ትጥቅ በመፍታት፣ በሪፎርም እና በትብብር ብቻ መሆኑን፤ ይህም የመንግስታቸው አቋም እንደሆነ በድጋሚ ግልፅ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “በፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የተመደበው በጀት ሙሉ በሙሉ በልማት ላይ ሳይሆን ለወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እየዋለ ነው፤ ይህም ትክክል አይደለም” ብለዋል። ትግራይ “ልማት እንደሚያስፈልጋትና ለዚህም በሰላማዊ መንገድ መሥራት እንዳለባት” አጽንዖት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የህወሓትን “ሕገ-ወጥ ክልላዊ ምክር ቤት እና አስተዳደር” እንዲፈርስ የሚያካትት እንደነበረ አስታውሰው “እነዚህም በሕገ-ወጥ ምርጫ የተቋቋሙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በሰላም ስምምነቱ መሠረት ሁሉንም የፖለቲካ ተዋናዮች ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ጥሪ መደረጉን” ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ህወሓት የሰላም ሂደቱን የሚያሰናክሉ እንደ የጦር መሳሪያ ኮንትሮባንድ ማዘዋወር እና ያልተፈቀደ የውጭ ግንኙነት መፈጸም ያሉ ተግባራትን ቀጥሏል” ሲሉም ከሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት፣ የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ስለሚደረጉ ጥሪዎች አስተያየት ሰጥተዋል። ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን በከፍተኛ ድምፅ የሚጠይቁት አካላት አንዳንዶቹ “የድርድሩ ሂደት አካል አልነበሩም” ሲሉም ተናግረዋል።

“ፕሪቶሪያን የተደራደርነው ከጄነራል ጻድቃን፣ ጌታቸው ረዳ እና አሰፋ አብርሃ ጋር ነው። ዋነኞቹ ተደራዳሪዎች እነዚህ ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “እነሱን ስጠይቃቸው ያሉኝ ነገር አለ። ነገር ግን በቦታው ያልነበሩት ፕሪቶሪያን የማያውቁት ሰዎች ፕሪቶሪያን እናስከብራለን ይላሉ። የወለደችው እያለች የታቀፈችው እናት ልሁን አለች እሱ ነው” ብለዋል።

ቀጠል አድርገውም “ፕሪቶሪያ ስምምነቱ አንደኛ ህወሓት ህጋዊ ምርጫ አላደረገም ህገመንግስት ጥሶ ነው ያካሄደው ያን የጨበራ ምርጫ ይሰርዝ፤ ሁለተኛ በዚያ ምርጫ የተቋቋመው መንግስት ይፍረስ ምክር ቤቱ ይበተን ህጋዊ ምክር ቤት አይደለም፤ ሶስተኛ ከሁሉ የተውጣጣ መንግስት ይመረጥ፤ የታጠቀ ትጥቁን ይፈታል እንጂ መሳሪያ መደበቅ አልተስማማንም፤ ማሰልጠን ማስመረቅ አልተስማማንም” ሲሉ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ሲናገሩም፣ ቡድኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገና በመመዝገብ ሕጋዊነቱን መመለስ እንደሚችል ገልጸዋል።

አያይዘውም ህወሓት በዋነኝነት የሚጠበቅበት የምርጫ ቦርድን ማክበር፣ ሕገ-መንግሥቱን ማክበር እና ሕጋዊ ፓርቲ ለመሆን ጉባኤ ማካሄድ ነው። ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ነገር አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የምርጫ ቦርድ ሕወሓት ደረጃውን ለማሟላት ቦርዱ ያዘዘውን “የማስተካከያ እርምጃዎች” በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድን ጨምሮ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት መሻሩ ይታወቃል።

በወቅቱ ሕወሓት ውሳኔውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ የፓርቲው ህጋዊነት የተረጋገጠው በፕሪቶሪያው የጦርነት ማቆም ስምምነት እንጂ በምርጫ ቦርድ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ማዕቀፍ እንዳልሆነ ተናግሯል። ፓርቲው እገዳውን ተከትሎ ከዚያ በኋላ የተሰጠውን ስረዛ “በህግ ደረጃ ትርጉም የለሽ” ሲል ቀደም ሲል ውድቅ አድርጎ ነበር። አስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...