ዓለም አቀፍ ድጋፍ በመቀነሱ ቢያንስ በ70 አገራት የሚኖሩ ዜጎች የህክምና አገልግሎት እያጡ ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም እንዳሉት በድጋፍ መቀዛቀዝ ሳቢያ ታካሚዎች ከኪሳቸው አውጥተው ለመታከም በመገደዳቸው በቂ የህክምና አገልግሎት እያገኙ አይደለም የጤና ተቋማትም ተዘግተዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በበርካታ የድጋፍ ሰጪ ተቋማት የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎችም የስራ ውላቸው ተቋርጦ ቤት ለመቀመጥ ተገደዋል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከአጠቃላይ ዓመታዊ በጀቱ የ600 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት እንደገጠመው የገለጸ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚተገብራቸውን 21 በመቶ ስራዎቹን ለማጠፍ መወሰኑን አስታውቋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የድርጅቱ ዋነኛ የገንዘብ ለጋሽ የነበረችው አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ድጋፏን ለማቋረጥ መወሰኗ ይታወሳል፡፡
